በየክልሉ ግንባታቸው የተጓተቱ ስታዲየሞች እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በየክልሉ ግንባታቸው የተጓተቱ ስታዲየሞች እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራል
አሶሳ፤ ነሐሴ 20/2017 (ኢዜአ)፦ በየክልሉ ግንባታቸው የተጓተቱ ስታዲየሞች እንዲጠናቀቁ እንደሚሰራ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ተናገሩ።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሸርቆሌ ወረዳ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ያከናወነ ሲሆን በአሶሳ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ተመልክተዋል።
በምልከታው ወቅት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እንደተናገሩት፤ መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ ልማት በሰጠው ትኩረት በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እየተገነቡ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው የዘገየ ስታዲየሞች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረት በመስጠት የግንባታ ስራቸው እንዲከናወን በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአህመድ ናስር መታሰቢያ ስታዲየም ግንባታ በተጀመረው የስራ እንቅስቃሴ ልክ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ዕገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በየአካባቢው እንዲስፋፉ ማድረግ ታዳጊዎች ስፖርትን ባህል እንዲያደርጉና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያግዛል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን በበኩሉ ክልሉ ለሁሉም ስፖርቶች ምቹ በመሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን በማስፋት ታዳጊዎች ላይ መስራት ይጠበቃል ብሏል።
ፌዴሬሽኑ በክልሉ ወንበራ ወረዳ የአትሌቲክስ ፕሮጀክት እንዳለው ገልጾ ለስፖርቱ ተስማሚ የአየር ሁኔታ በመኖሩ የአልማዝ አያናን ተተኪዎች ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ተናግሯል።