ሊቨርፑል ድል ቀንቶታል 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሊቨርፑል ኒውካስትል ዩናይትድን 3 ለ 2 አሸንፏል።

ትናንት ማምሻውን በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ራያን ግራቨንበርች በ35ኛው እና ሁጎ ኢኪቲኬ በ46ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ባሰረፏቸው ግቦች ሊቨርፑል መሪ ሆኖ ነበር።

ብሩኖ ጉማራይሽ በ57ኛው እና ዊሊያም ኡሱላ በ88ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ግቦች ኒውካስትልን አቻ አድርጓል። 

ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል ተቀይሮ የገባው የ16 ዓመቱ ሪዮ ኢንጉሞሃ በጭማሪ ደቂቃ 100ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል ለሊቨርፑል ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስገኝቷል። ታዳጊው በመጀመሪያ የሊግ ጨዋታው ግብ ማስቆጠር ችሏል።

የኒውካስትል ዩናይትዱ አጥቂ አንቶኒ ጎርደን በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ በቨርጂል ቫንዳይክ ላይ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ይህም ባለሜዳው ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ በ10 ተጫዋች እንዲጫወት አስገድዶታል።

በጨዋታው ላይ ከሊቨርፑል ጋር በዝውውር ስሙ የተያያዘው የኒውካስትሉ አጥቂ አሌክሳንደር አይዛክ ጉዳይ ከጨዋታው በላይ ትኩረትን ስቧል። ተጫዋቹ በጨዋታው ላይ አልተሰለፈም።

ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ በስድስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ኒውካስትል ዩናይትድ በአንድ ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዟል።

በሶስተኛ ሳምንት ሊቨርፑል ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ኒውካስትል ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም