ቀጥታ፡

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስፈላጊውን የጥራት መስፈርት ሊያሟሉ ይገባል-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፡-የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት ዳግም ምዝገባ ሊያደርጉ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

ትምህርት ሚኒስቴር እና የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዳግም ምዝገባ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት አካሂደዋል።


 

በመድረኩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዳግም ምዝገባ ውጤት ይፋ ሆኗል።

የተሟላ ህጋዊ ሰነድ፣ ንግድ ፍቃድ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ የመምህራን ብቃት እና የሰው ኃይል፣ የሚያስተምሩበት የህንጻና አካባቢ ሁኔታ፣ የመረጃን ዲጂታላይዜሽን እና ሌሎች መስፈርቶች መታየታቸውን ተነስቷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት፥ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም ምዝገባ በማካሄድ የጥራት መስፈርትን  እንዲያሟሉ አሳስበዋል።  

መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ብቁ እና ተወዳዳሪ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለብቁ የሰው ኃይል ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፥ ሆኖም ተመዝነው ብቃት የሌላቸው ተቋማት ጥናትን መሰረት በማድረግ ከትምህርት ስርዓቱ እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በመሆኑም ተቋማቱ ከገንዘብ ባለፈ ለትውልድ ግንባታ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር፤ የሁሉም የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መረጃ የሚመዘገብበት የመረጃ ቋት  አልምቶ በስራ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ተቋማቱ አንድ ላይ በመሰባሰብ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚችሉ ጠቁመው ሚኒስቴሩም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


 

የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አህመድ አብተው(ዶ/ር) በበኩላቸው በየጊዜው ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በዳግም ምዝገባ እና አስፈላጊነቱ ላይ ውይይት ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ተገቢውን መስፈርት እንዲያሟሉ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቷቸው መቆየቱን ጠቅሰው፥ በዚህም መሻሻል ያሳዩ ተቋማት መኖራቸውን አስረድተዋል።

ሁሉም ተቋማት ሙሉ መረጃቸውን በሲስተሙ ላይ የማስመዝገብ ግዴታ አለባቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የጥራት መስፈርት ያላሟሉት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ በተካሄደው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም ምዝገባ እና የጥራት መስፈርት ማረጋገጫ መሰረት ውስን ተቋማት መስፈርቱን ማሟላታቸውን የገለፁት በባለሥልጣኑ የከፍተኛ ትምህርት ፍቃድ አሰጣጥ መሪ ስራ አስፈጻሚ ህይወት አሰፋ ናቸው።


 

መስፈርቱን ያላሟሉ ተቋማት ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲያሟሉ የጊዜ ገደብ እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የግል ትምህርት ተቋማት ማህበር ስራ አስኪያጅ ተፈራ ገበየሁ በበኩላቸው ተቋማቱ ለዳግም ምዝገባ ራሳቸውን በተሟላ ሁኔታ ማዘጋጀት እንዳለባቸው አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም