በቻይና የተካሄደው የክህሎት ውድድር ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያሳየችበት ነው - የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና የተካሄደው የክህሎት ውድድር ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያሳየችበት ነው - የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፡- በቻይና የተካሄደው የክህሎት ውድድር ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ያሳየችበት መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ኢትዮጵያን በመወከል በውድድሩ ያሸነፉት ተወዳዳሪዎች ሀገራችን በክህሎት ልማት ላይ እየሰራች እንዳለ በዓለም የክህሎት አደባባይ ያረጋገጡበት እንደሆነም ገልጸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በቻይና በተካሄደ የክህሎት ውድድር አሸናፊ የሆኑትን ወጣቶች በቢሯቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ከብሪክስ አባል ሀገራት ከተውጣጡ ከ300 በላይ የተሳተፉበት የቻይና የክህሎት ውድድር ኢትዮጵያዊያን የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነዋል።
ለ11ኛ ዙር በቻይና ጎዋንዡ በተካሄደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ከተወዳደሩት ወጣቶች መካከል ዘላለም እንዳለው 1ኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ፣ አቤኔዘር ተከስተ 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን፤ ነቢሀ ነስሩ 3ኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከለውጡ ወዲህ መንግስት በክህሎት ልማት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።
በዚህ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ እንዳለ አንስተው፤ በዓለም አደባባይ በመወዳደር ሀገርን ማስጠራት እየተቻለ ነው ብለዋል።
በቻይና የተካሄደው የክህሎት ውድድር ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ያሳየችበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሌሎች ወጣቶች ክህሎታቸውን በማውጣት እና ተቋማት በጋራ መስራት ከቻሉ የበለጠ ውጤት እንደሚያመጡ ገልጸዋል።