መገናኛ ብዙሀን ብሔራዊ ጥቅምን ዋነኛ አጀንዳ አድርገው መስራት ይገባቸዋል-ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙሀን ብሔራዊ ጥቅምን ዋነኛ አጀንዳ አድርገው መስራት እንደሚገባቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለፁ።

"መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም እና ለሰላም'' በሚል መሪ ሀሳብ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን 30ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማስመልከት የተዘጋጀ አውደ ጥናት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

ዶክተር በቂላ ሁሪሳ በአውደ ጥናቱ ላይ ''ሚዲያ ለብሔራዊ ጥቅም'' በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙሀን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው መስራት ይገባቸዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በሁለንተናዊ መንገድ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉዳዮችን የአጀንዳዎች ሁሉ የበላይ አጀንዳ አድርገው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ነው የገለጹት።

በዚህም ኢትዮጵያ ሰላሟ የተረጋገጠ፣ ከድህነት ለመውጣት የምትጥር፣ በራሷ አቅም ሉአላዊነቷንና ነፃነቷን አረጋግጣ ተከብራ የምትኖር ሀገር መሆኗን ማሳየት አለባቸው ብለዋል።

የክልልም ሆነ ብሔራዊ ሚዲያዎች ከነጠላ ትርክት ወጥተው የጋራ ትርክት ግንባታ ላይ በማተኮር ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጥቅሟን እንድታስከብርና አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ጠንክረው እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።

ሚዲያዎች ሀገርን ሊያሻግሩ በሚችሉ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት አድርገው መስራት ይገባቸዋል ያሉት ደግሞ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ናቸው።

በተለይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ በተደራጀና ተከታታይነት ባለው መንገድ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው መስራትና ማሳወቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት ለአሰባሳቢ አጀንዳዎች ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ፈጠራ በታከለበት መንገድ ተደራሽ ማድረግ ከሚዲያዎች ይጠበቃል ብለዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የህዝብ ድምጽ በመሆን የተጣለበትን ሃላፊነት እየተወጣ ይገኛል ያሉት ደግሞ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉቀን ሰጥየ ናቸው።

አሚኮ ከህዝብ የሚነሱ ችግሮችን ማሳየት ብቻ ሳይሆን መፍትሄ እንዲያገኙ የተለያዩ የአሰራር ስልቶችን በመተግበር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ ሰላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደርን የተመለከቱ ሥራዎች እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ኮርፖሬሽኑ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ቀጣይ ሃገራዊ አንድነት በሚፈጥሩና ብሔራዊ ጥቅሞችን በሚያረጋግጡ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሥራዎች እንደሚሰሩም ነው አቶ ሙሉቀን ያሳወቁት።

አሚኮ በክልሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ አበክሮ በመስራት አሻራውን እየጣለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ ናቸው።

በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ የተጣሉበትን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጣና የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ህዝቡ የሚጠበቅበትን እገዛ ማድረግ እንዳለበትም አፈጉባኤው አመልክተዋል።

የፌደራልና የክልል አመራሮች በተገኙበት በዚህ መድረክ ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸው ሲሆን የአሚኮ የ30ኛ ዓመት በዓልም በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም