ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የወጣቶችን የፈጠራ አቅም በመጠቀም አፍሪካዊ ትብብርን ማጎልበት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የወጣቶችን የፈጠራ አቅም በመጠቀም አፍሪካዊ ትብብርን ማጎልበት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በፓን አፍሪካ የአየር ንብረት ፍትህ ጥምረት የተዘጋጀው 5ኛው የ2025 የአየር ንብረት ፍትህ የናይሮቢ የክረምት ትምህርት መርሐ ግብር በአዲስ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤  የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከመሰባሰብ ባለፈ የተግባር ርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

የናይሮቢ የአየር ንብረት ለውጥ የክረምት ትምህርት መርሃ ግብር ዓለም በፈታኝ የአየር ንብረት ለውጥ ውስጥ ባለችበት ወቅት የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የወጣቶችን አቅም በመጠቀም ያምናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ቀጣይነት ያለውና የተሻለ ዓለምን ለመፍጠር የወጣቶች ሚና የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

የወጣቶች መሰባሰብ ችግሩን ለመከላከል ብሩህ ተስፋ የሚሰንቅ መሆኑን ገልጸው፤ ከመምከር ባሻገር ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ የተግባር እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ የወጣቶችን የፈጠራ አቅም በመጠቀም አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡


 

የፓን አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ፍትሕ ጥምረት ዋና ዳይሬክተር ሚቲካ ምወንዳ፤ አፍሪካ በወረርሽኝ፣ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ውስንነት የሚፈትኗት አህጉር መሆኗን ገልጸዋል።

የናይሮቢ የአየር ንብረት ለውጥ የክረምት ትምህርት አፍሪካ እያስተናገደች ያለውን ችግር መቋቋም የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳብ ለማፍለቅ ያግዛል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል የወጣቶች ሚና የጉላ መሆኑን በመግለጽ፤ ተሳትፏቸውን ማሳደግ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታሳድረው ጥቂት ሆኖ ብዙውን ተጎጂ መሆኗን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይሄውም ዓለም አቀፉ ስርዓት የፈጠረው ከብረነክነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በአፍሪካ የአየርን ንብረት ለውጥ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ዜጎች በድርቅና ረሃብ እንደሚጠቁ ገልጸው፤ ችግሩ የተከሰተው በአደጋ ሳይሆን በመንግሥታት ፖለቲካዊ ምርጫ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡

የአየር ንብረት ፍትህ ረቂቅ ጉዳይ ሳይሆን ዜጎች ህይወታቸውን ለማስቀጠል በየቀኑ የሚጋፈጡት ነባራዊ እውነታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ኮምፒቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ቢቂላ ወርቅነህ (ዶ/ር)፤ አምስተኛው የአየር ንብረት ፍትህ የናይሮቢ የክረምት ትምህርት መርሐ ግብር የሁለተኛው የአፍሪካ የአየርን ንብረት ጉባኤ ቅድመ ጉባኤ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያከናወነቻቸው በርካታ ሥራዎች ልምድ የምታካፍልበት መድረክ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ከዓለም ማዕዘናት ከመጡ ሌሎች ወጣቶች ጋር የሚማማሩበት፤ ሌሎች ደግሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የሚሆኑበትን እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም