ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ገቢራዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ለውጥ አስመዝግባለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ገቢራዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ለውጥ አስመዝግባለች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቀነስ የሚያስችል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ገቢራዊ በማድረግ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ማስመዝገቧን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በፓን አፍሪካ የአየር ንብረት ፍትህ ጥምረት የተዘጋጀው አምስተኛው የ2025 የአየር ንብረት ፍትህ የናይሮቢ የክረምት ትምህርት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የናይሮቢ የአየር ንብረት ለውጥ የክረምት ትምህርትን ማዘጋጀቷ ታላቅ ኩራት ነው።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የተለያዩ የፖሊስ ርምጃዎች በወሰደችበት እና ሁለተኛውን የአየር ንብረት ጉባኤ በምታስተናግድበት ወቅት በመሆኑ ክብር ይሰማናል ብለዋል።
በመርሀ ግብሩ ከ141 የዓለም ሀገራት የተወጣጡ የአየር ንብረት ለውጥ ወጣት መሪዎች የታደሙበት መሆኑን በመጥቀስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በየዓመቱ ከሁለት እስከ አምስት በመቶ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት እንደሚያሳጣ በመግለፅ፣ በአፍሪካ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ከአራት በመቶ የማይበልጥ ዝቅተኛ አስተዋፅኦ ቢኖራትም የጎላ ጉዳት እንደምታስተናግድ ገልጸዋል።
የዓለም የአየር ንብረት ፋይናንስ ስርዓት ለማስተካከል ለአፍሪካውያን ትብብር፣ ቁርጠኝነት፣ ፍትሐዊነት እና ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ መፍትሄ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በዘላቂነት ለመፍታት አፍሪካውያን አፍሪካዊ መፍትሔ መፈለግ ይገባናልም ብለዋል።
በዚህም በሀገር በቀል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስርዓት ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ ርምጃ በመውሰድ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸው፤የአየርን ንብረት ለውጥን ከፓሪስ ስምምነት ቀድማ ርምጃ መውሰድ መጀመሯን ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት በ2011 ዓ.ም በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ2018 ዓ.ም 50 ቢሊዮን ችግኞችን ታቅዶ እስካሁን ከ48 ቢሊዬን በላይ መድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች 50 ሚሊዬን ሄክታር የተራቆተ መሬት መመለስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ 96 በመቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከታዳሽ ኃይል እንደምታመነጭ ገልጸው፤ ውጤቱ የሀይል ሽግግር ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን የኃይል ማመንጫ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመጭው መስከረም እንደምታስመርቅ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የሚያመነጨው ኃይል ኢትዮጵያን ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያስተሳስራል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ ከ60 በላይ ከተሞችን በኮሪደር ልማት ምቹና አረንጓዴ እያደረገች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የብስክሌት የአካል ጉዳተኞችና ሌሎችን የአረንጓዴ ትራንስፖርትን የሚያበረታቱ መሰረተ ልማቶች ተካተውበታል ብለዋል፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የኢትዮጵያን መልክ የሚገልጹ፣ የተፈጥሮ ሚዛንን የሚጠብቁ፣ ውብ ከባቢን የሚፈጥሩ ሰው ተኮር ስራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከውጭ ስንዴ በማስገባት የምትታወቅበትን የዘመናት ታሪክ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ማስዝገቧንም ጠቅሰዋል፡፡