በኢትዮጵያ ግብርናን ከዝናብ ጠባቂነት የሚያሻግር የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የግብርና ሥርዓት ከዝናብ ጠባቂነት አሰራር የሚያሻግር የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ሀገር አቀፍ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥራት የሚያስጠብቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ስታንዳርድ ዝግጅት አውደ ጥናት የማጠናቀቂያ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።


 

በዚሁ ጊዜም የኢትዮጵያን የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥራት በማስጠበቅ ወጥ የሆነ አሰራርን የሚፈጥር የመስኖ ፕሮጀክቶች የማስፈጸሚያ ስታንዳርድ የሰነዶች ርክክብ ተደርጓል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ካልተቻለ የሀገርን የተሟላ ሉዓላዊነት ማጎናጸፍ አይቻልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በግብርና ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የመጣችበት መንገድ በዝናብ ጥገኝነት የተመሰረተና የመስኖ ፕሮጀክቶችም ወጥነት የጎደላቸው እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን በዝናብ ላይ የተንጠለጠለ የግብርና ሥርዓት ለማስተካከል የተለያዩ የመስኖ ልማት አማራጭ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም ወጥ የሆነ የመስኖ ልማት ፍኖተ ካርታ አለመኖሩም በፕሮጀክት አፈፃጸም ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር እንደቆየ አስረድተዋል።

የመንግስት ሃብት አዋጭ በሆነ ፕሮጀክት ላይ መዋል አለበት ያሉት ሚኒስትሩ÷ ለዚህም ጥራታቸውን የጠበቁ የመስኖ ፕሮጀክቶች መገንባት የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጦ እተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በዚህም ሰነዱ በአዋጭነት ጥናት ላይ የተመሰረተ የመስኖ ፕሮጀክት የልማት ስራዎችን በታወቀ የአሰራር ሥርዓት ማከናወን የሚያስችል አካሄድ መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።


 

በመንግስታቱ ድርጅ የምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ÷ የመስኖ ልማት የፕሮጀክቶች ጥራት ማስጠበቂያ ሰነድ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የመስኖ ልማት ጥራት ክፍተቶችን በመሙላት በዘመናዊ መመሪያና የቴክኒክ ደረጃዎች እንዲመራ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት የምግብና ግብርና ምርታማነት ዘላቂነትን በመደገፍ ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሌለበትን ዓለም የመፍጠር ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአባል ሀገራትን ዘላቂ የልማት ግብ ለማሳካት የግብርና ምርታማነትን የሚያሳልጥ ስትራቴጂካዊ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።


 

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ÷ የመስኖ ስታንዳርድ ማስፈጸሚያ ደንብ መዘጋጀቱ በፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለማረም ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር)÷ የመስኖ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ስታንዳርዱን በመስኖ የሚለማውን የመሬት ሃብት ታሳቢ በማድረግ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።


 

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን መሪ ሥራ አስፈፃሚ ያሬድ ሙላቱ÷ ኢትዮጵያ በፕሮጀክቶች አፈፃጸም የሚያጋጥማትን እክል የሚያርም የመስኖ ፕሮጀክቶች ስታንዳርድ ባለቤት ሆናለች ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና የመስኖ ፕሮጀክቶች ስታንዳርድ ጥናት አስተባባሪ በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያን የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥራትና ደኅንነት የሚያስጠብቁ 26 የመስኖ ፕሮጅት ስታንዳርዶች ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።


 

በመስኖ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ስታንዳርድ በመንግስታት ድርጅ የምግብና እርሻ ድርጅት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም በአዲስ አበባና አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ትብብር መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም