ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መገለጫ በመሆኑ ሁሌም የምንኮራበት ፕሮጀክት ነው

ነገሌ ቦረና፤ነሀሴ 19/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መገለጫ በመሆኑ ሁሌም የምንኮራበት ፕሮጀክት ነው ሲሉ የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ መላ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነትና በአብሮነት ለዘላቂ ልማትና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ እንደሆነም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ 


 

የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ መምህር አስማማው ሀይሉ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ነው የገለጹት።

የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና የይቻላል መገለጫ በመሆኑ ሁሌም የምንኮራበት ፕሮጀክት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሀይለኢየሱስ ዳባ፤ የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በማሳካት ተጨማሪ ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ያሳዩበት ነው ብለዋል።

ለግድቡ ግንባታ በተለያየ ጊዜ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ግድቡ በቅርቡ እንደሚመረቅ ዜናውን ሲሰሙ የተለየ ደስታ እንደተሰማቸውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በፍላጎትና በተነሳሽነት ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ያደረጉለት ፕሮጀክት ዛሬ ለፍሬ በቅቶ በማየታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ታምራየሁ ታምራት ናቸው። 

የግድቡ ግንባታ የህዝብን አንድነትና መተባበር ከማሳደግ ባለፈ የአይቻልም አመለካከትን መስበሩን ገልጸው፣ ለበለጠ ሥራ በጋራ መነሳት እንደሚቻልም ያመለከተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም