በክልሉ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያና የኮሪደር ልማት ስራዎች ለስፖርቱ እድገት ትልቅ ትርጉም አላቸው - ሳልሀዲን ሰኢድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያና የኮሪደር ልማት ስራዎች ለስፖርቱ እድገት ትልቅ ትርጉም አላቸው - ሳልሀዲን ሰኢድ
አሶሳ፤ ነሐሴ 19/2017 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያና የኮሪደር ልማት ስራዎች ለስፖርቱ እድገት ትልቅ ትርጉም ያላቸው መሆኑን የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጨዋች ሳልሀዲን ሰኢድ ገለጸ።
የልማት ስራዎቹ ለስፖርቱ እድገትና ማንሰራራት መንግስት የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳዩ መሆናቸውንም ተናግሯል።
በክልሉ ሰሞኑን በመገኘት የተለያዩ የልማት ስራዎችን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ሆነ የአሶሳ ከተማ እየተለወጡ ያለበት መንገድ የሚታይ መሆኑን መግለፃቸው ይታወቃል።
በክልሉ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማዋ የተሰሩ እና በሂደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የላቀ ትርጉም ያላቸው መሆኑም ተመላክቷል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጨዋች ሳልሀዲን ሰኢድ፤ የክልሉን የልማት እንቅስቃሴዎችን አድንቋል።
በሀገር ውስጥ ለሙገር ሲሚንቶ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለሲዳማ ቡና ከውጪ ደግሞ ለግብጽ እና አልጄሪያ ክለቦች ተጨውቶ አሳልፏል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግርኳስ ተጨዋች ሳልሀዲን በተጨዋችነት ዘመኑ ለእረፍት ወደ ትውልድ ቦታው አሶሳ ከተማ በሚመጣበት ጊዜ ለልምምድ የሚሆን የማዘውተሪያ ቦታ እንዳልነበር ያስታውሳል።
በአሁኑ ወቅት በአሶሳ የአህመድ ናስር መታሰቢያ ስታዲየምን ጨምሮ ሌሎች መለስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሁም ለእንቅስቃሴ ምቹ የሆነ የኮሪደር ልማት መከናወኑ እንዳስደሰተው ተናግሯል።
የልማት ስራዎቹ ለስፖርቱ እድገትና ማንሰራራት መንግስት የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳዩ ናቸውም ብሏል።
የአህመድ ናስር መታሰቢያ ስታዲየም ግንባታ በተጀመረው ልክ ግንባታው በጥራትና በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ እየተደረገ ያለው የተቀናጀ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን አንስቷል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከነበረው የብሄራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ በመሳተፍ ሳልሀዲን የታሪኩ አካል የነበረ ድንቅ ተጫዋች እንደነበር ይታወሳል።