የመስኖ ፕሮጀክቶችን በውጤታማ የአዋጭነት ጥናት መምራት የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ ፕሮጀክቶችን በውጤታማ የአዋጭነት ጥናት መምራት የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦የመስኖ ፕሮጀክቶችን በውጤታማ የአዋጭነት ጥናት መምራት የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት እየተፈጠረ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለጸ።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥራት የሚያስጠብቅ የመስኖ ስታንዳርድ ማስፈጸሚያ ደንብ የሰነድ ዝግጅት የአውደ ጥናት የማጠናቀቂያ የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
ስታንዳርዱ በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን የጥናት ትብብር መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በምክክር መድረኩ ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ፣ የሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተገኝተዋል።
በዚሁ ጊዜ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ፥ የመስኖ ፕሮጀክቶች ልየታ፣ የቅድመ አዋጭነትና የአዋጭነት ጥናት አቅምን በማሳደግ የመስኖ አስተዳደር ሥርዓትን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም የመስኖ ፕሮጀክቶችን ልማት ተቋማዊ የአሰራርና የአደረጃጀት ውጤታማነት የሚያጠናክር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የቅድመ አዋጭነት ጥናት ክፍተቶች በመስኖ ፕሮጀክቶች ልማት ላይ እንቅፋት ሲፈጥሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
የመስኖ ስታንዳርድ ማስፈጸሚያ ደንብ ሰነድ መዘጋጀቱም በፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በማረም ሀገራዊ ተልዕኮን ለመወጣት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በመስኖ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ሰነድ ዝግጅቱ በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም በአዲስ አበባና አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ምሁራን የጥናት ትብብር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ፥ የመስኖ ልማት የፕሮጀክቶች ጥራት ማስጠበቂያ ሰነድ የግብርና እና የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የመስኖ ልማት ጥራት ክፍተቶችን በመሙላት በዘመናዊ መመሪያና የቴክኒክ ደረጃዎች እንዲመራ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት የምግብና ግብርና ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ ዘላቂነትን በመደገፍ ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሌለበትን ዓለም የመፍጠር ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአባል ሀገራትን ዘላቂ የልማት ግብ ለማሳካት የግብርና ምርታማነትን የሚያሳልጥ ስትራቴጂካዊ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።