የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ውስጣዊ አንድነትና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ውስጣዊ አንድነትና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማጠናከር ይገባል

ባህርዳር ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ውስጣዊ አንድነትንና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለፁ።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽ(አሚኮ) 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ "መገናኛ ብዙሃን ለብሄራዊ ጥቅምና ለሰላም'' በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ አውደ ጥናት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) "ሚዲያ ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል ርዕስ በአውደ ጥናቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በዚህ ጽሁፋቸው እንዳመለከቱት፤ መላው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሁለንተናዊ መንገድ ለማስከበር በአንድነት ሊረባረብ ይገባል።
የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም የሚጎዳ ማንኛውንም እንቅስቃሴ በሀሳብ የበላይነት መሞገትና ማክሸፍም እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዚህም ውስጣዊ አንድነትና ሰላምን በማስጠበቅ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አቅምን ማጠናከርና የዲሞክራሲ አቅም በመገንባት መረባረብ እንደሚገባ አብራርተዋል።
መንግስት የኢትዮጵያን ብልፅግና በሁለንተናዊ መንገድ ለማረጋገጥ በሁሉም መስክ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በመሆኑም መገናኛ ብዙሀን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ላይ አጀንዳ ፈጥረው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በአውደ ጥናቱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤን ጨምሮ ሌሎችም የስራ ሀላፊዎች እየተሳተፉ ሲሆን፤ በቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።