የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስና ገበያን ለማረጋጋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስና ገበያን ለማረጋጋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስና ገበያን ለማረጋጋት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የገበያ ማረጋጋት፣ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥርና የኢትዮጵያ-አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ግብረ ኃይል የበዓል ገበያንና ከዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ መግለጫ ሰጥቷል።
በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ እንዳሉት በከተማዋ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያን ለማረጋጋት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ አቅርቦትን ለማስፋት የተለያዩ ስራዎችን እየተገበረ መሆኑን አንስተው ሁለት መቶ አስራ ዘጠኝ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እንዲሁም አምስት የገበያ ማዕከላት ለሸማቾች ምርቶችን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና በመንግስት ሰራተኞች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለዚህም አስራ አራት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር ድጎማ በመመደብ የተማሪዎች ምገባ፣ ጤና መድህን፣ ሸገር ዳቦ እንዲሁም ሌሎች የኑሮ ጫናን ለመጋራት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
የገበያ ማረጋጋት፣ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥርና የኢትዮጵያ-አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄን የሚመራ ግብረ ኃይል ተደራጅቶ ወደስራ መግባቱን ጠቁመው ግብረኃይሉ በየጊዜው የአቅርቦት አማራጮችና መጠንን ለማስፋት እየሰራ ነው ብለዋል።
ግብረ-ሀይሉ ገበያን በማረጋጋት እና ህገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ህብረተሰቡ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ግብረኃይሉ በየጊዜው በግብይት ማዕከላትና በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ያለውን ሽያጭ በመቆጣጠር የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር የማድረግ ስራን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በማህበራትና ገበያ ማዕከላት ምርቶች ከአስራ አምስት እስከ ሃያ በመቶ ቅናሽ ባለው ዋጋ ለህብረተሰቡ እየቀረቡ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
በዓላትንና የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ጭማሪን አስመልክቶ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የአቅርቦትና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ የህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ መረጃ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።