በኢትዮጵያ የትምህርት ምዘና ስርዓቱ ላይ እየተካሄደ ያለው ለውጥ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በጎ ሚና እየተጫወተ ነው - ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የትምህርት ምዘና ስርዓቱ ላይ እየተካሄደ ያለው ለውጥ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በጎ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ። 

"የትምህርት ምዘናን ለማሸጋገር ጥራት ያለው ትምህርትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው 41ኛው የአፍሪካ ትምህርት ምዘና ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። 

ጉባኤው በአባል ሀገራት መካከል ጠንካራና ተዓማኒነት ያለው የትምህርት ምዘና ስርዓት መገንባት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል። 


 

በትምህርትና ምዘና ስርዓት ዙሪያ ያሉ እሳቤዎች፣ቴክኖሎጂዎች፣ልምዶችና ተሞክሮዎች የሚቀርቡ ሲሆን በዘርፉ ፍትሀዊ አሰራርን ለማስፈን የሚያስችል ምቹ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስር መፍጠር የሚያስችል ምክክር እንደሚደረግም ተገልጿል። 

በምዘናና ፈተና ዓለም አቀፍ ተሳትፎን ማሳደግ፣ በምርምር የታገዘ የትምህርትና ምዘና ስርዓት ማንበር፣ ዘላቂ ትብብር መፍጠር፣ በጋራ መስራት ከጉባኤው ከትኩረት መስኮች መካከል ናቸው።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ለውጥ ላይ መሆኗን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ አፍሪካን ያቀፈ ለውጥ ለማረጋገጥ በግብርና፣ በኃይል ልማት፣ መሰረተ ልማትና ትምህርት ዘርፍ ላይ እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል። 

የትምህርት ምዘና ስርዓቱ ላይ እየተካሄደ ያለው ለውጥ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር በጎ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል። 

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ምዘና ላይ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መሥጠት የትምህርት ምዘናን ለማሻሻል ትልቅ መፍትሔ ነው ብለዋል። 


 

በኢትዮጵያ የትምህርት ምዘና ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል። 

የዓለም ስልጣኔ ለውጥ ላይ በመሆኑ የአፍሪካን ቀጣይ መዳረሻ ማሰብና መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ጥራት ያለው ትምህርት አፍሪካን እንደሚያሻግርም ተናግረዋል። 

የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) የትምህርት ምዘና ለአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ውጤታማነት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። 

ስራው ስኬታማ እንዲሆንም ቀጣይነት ባለው መልኩ በቅንጅት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ነው በአዲስ አበባ የሚካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም