አፍሪካን የመጪው ዘመን መሪ ለማድረግ ለትምህርት ጥራት ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦አፍሪካን የመጪው ዘመን መሪ አህጉር ለማድረግ ለትምህርት ጥራት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማህበር 41ኛ ዓመታዊ ጉባኤ "የትምህርት ምዘናን ማዘመን" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፥ በመድረኩ የአህጉሪቱ የትምህርት ምዘና የጋራ ማዕቀፍ ይፋ ሆኗል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጉባኤው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር በአፍሪካ እያንዳንዱ ልጅ የመማር ዕድል ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ የትምህርት ማህበረሰቡ በጋራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ምዘና መማርን የመለካት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ጠቅሰው፥ አሁናዊ ቁመናን በመረዳት ቀጣይ መዳረሻን የሚመራ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማህበር ለትብብር፣ ለእውቀትና ለፈጠራ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህም የአፍሪካን ትምህርት በጋራ ከፍ እናደርገዋለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የዓድዋ የድል መንፈስ አፍሪካውያንን ከጭቆና ነፃ እንዳወጣቸው በማውሳት፥ በትምህርት መስክ ሊደገም ይገባል፤ ምክንያቱም ትምህርት የነፃነት፣ የክብርና የዘላቂ ብልፅግና መሠረት ነው ብለዋል።


 

የአፍሪካ ሀገራት በትምህርት ላይ ጠንካራ ማሻሻያ እያደረጉ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያም የትምህርትና የምዘና ስርዓቷ ፍትሐዊ፣ ትርጉም ያለው እና በንድፈ ሀሳብ እውቀት ብቻ ሳይሆን በተግባር ክህሎቶች ላይ ያተኮረ እንዲሆን በጥልቀት በማሻሻል ላይ ትገኛለች ነው ያሉት። 

ለአፍሪካ የጋራ አህጉራዊ የትምህርት ምዘና ማዕቀፍ የመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት አለብን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የትምህርት ስርዓቱን ወጥ በማድረግ ተማሪዎች እና መምህራን ድንበር ዘለል የእውቀት መጋራትን እንዲፈጥሩ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

አፍሪካ እያደገች መሆኗን በማንሳት የበለጠ ማደግና መሪ መሆን ይገባታል፤ ለዚህም ጠንካራ፣ ፍትሃዊ እና እምነት የሚጣልባቸው የትምህርትና የምዘና ስርዓቶችን መፍጠር ይገባል ብለዋል።

የተማሪዎችን አቅም የሚያሳድጉ፣ የሀገራትን ጥረት የሚያጠናክሩ እና በአፍሪካ ብልጽግናን የሚያፋጥኑ የትምህርት ስርዓቶችን ለመፍጠር መትጋት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም