አሚኮ ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ ታግዞ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመዝለቅ የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
አሚኮ ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ ታግዞ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመዝለቅ የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ ቀጥሏል

ባሕርዳር፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፡- አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ ታግዞ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ሆኖ ለመዝለቅ የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠሉን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ሰጥዬ ተናገሩ።
''መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም እና ለሰላም'' በሚል መሪ ሀሳብ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን(አሚኮ) 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ አውደ ጥናት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ ላይ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤን ጨምሮ ሌሎችም የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
የአሚኮ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሉቀን ሰጥዬ እንደገለጹት፤ አሚኮ ችግሮችን በመቋቋም አሁን ያለበት የእድገት ደረጃ የደረሰ የሚዲያ ተቋም ነው።
በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ቋንቋዎችን በመጠቀም በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን ፣ በጋዜጣ እና በሌላውም የመገናኛ ዘዴ የሕዝብ ድምጽ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።
አሚኮ የክልሉን ገፅታ ከመገንባት ባሻገር በሰላም ግንባታ፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ የበኩሉን መወጣቱን አንስተዋል።
ምሁራን፣ አርሶ አደሩና ሌላው ሀሳብ ያለው ማሕበረሰብ ሁሉ ችግሩን፣ ልምድ፣ ተሞክሮውንና ሀሳቡን በነፃነት የሚገልፅበት ሚዲያ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሕዝብ ድምፅ ሆኖ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን ይዞ መዝለቅ የሚያስችለውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ በበኩላቸው ፤ አሚኮ በሰላምና ገፅታ ግንባታ እንዲሁም በልማትና መልካም አስተዳደር ዘርፎች በተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፋት 30 ዓመታት ችግሮችን ተቋቁሞ በሕዝብና መንግስት መካከል ድልድይ ሆኖ ያገለገለ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይም በቴክኖሎጂ ታግዞ የልሕቀት ማዕከል ሆኖ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በአውደ ጥናቱ "በቀውስ ወቅት የሚዲያ ሚና" እና "ሚዲያ ለብሔራዊ ጥቅም" የሚሉ ጹሁፎች እየቀረቡ ይገኛል።