በአማራ ክልል ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ጥጥ እየለማ ነው

ባህርዳር ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የጥጥ  ምርት እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኤልያስ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት ተኪ ምርትን በጥራትና በብዛት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ጥጥ በሀገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።


 

ለዚህም በ2017/18 የምርት ዘመን በክልሉ ለጥጥ ምርት ተስማሚ በሆኑ ቆላማ አካባቢዎች ለማልማት በዕቅድ ከተያዘው 81 ሺህ 392 ሄክታር መሬት 58 ሺህ 111 ሄክታሩ መልማቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 11 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ በተሰማሩ ባለሃብቶች፣ ቀሪው ደግሞ በአርሶ አደሮች የለማ ነው።

ይህም ከውጭ ይገባ የነበረውን የጥጥ ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን የግብዓት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለማቃለል እንደሚያስችል አመልክተዋል።

በምርት ዘመኑ የጥራት ደረጃውን ያሟላ የጥጥ ምርት ተመርቶ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ ከክልል እስከ ወረዳ ባለሙያዎች ተመድበው ልዩ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን በእርሻ ኢንቨስትመንት ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሃብቱ ፅዱ፤ 260 ሄክታር መሬትን ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት በሚሆን የጥጥ ምርት እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ ያካበቱትን ልምድ በመጠቀም ምርቱን በጥራትና በብዛት አምርተው ለጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘንድሮም እያለሙት ካለው መሬት የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የጥጥ ምርት ሰብስበው ለገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም  የተዳመጠ ጥጥ ለጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ለማቅረብ ዕቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።


 

በዚሁ ዞን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ገድፍ የኋላ በበኩላቸው ዘንድሮ ከ5 ሄክታር የሚበልጥ መሬትን በጥጥ ለማልማት የአረም ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ምርቱም በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረው ምርቱን በጥራት ሰብስበው ጥጥን ለሚዳምጡ ባለሃብቶች በማስረከብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸውም አስረድተዋል። 

በምርት ዘመኑ በክልሉ በጥጥ እየለማ ከሚገኘው መሬት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ይሰበሰባል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም