በሐረሪ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 10 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል

ሐረር ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 10 ሚሊዮን ብር  መሰብሰቡን በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በተያዘው በጀት ዓመትም በክልሉ ለግድቡ ግንባታ 20 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትና በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ እንደገለጹት፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ ነው።

ግድቡ ብሔራዊ ኩራትና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ትልቅ ምልክት መሆኑንና ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ገጽታዋን እየገነባ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ስኬታማ ለማድረግ በክልሉ ለግድቡ የሚከናወኑ የተለያዩ የድጋፍ ስራዎች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።

የክልሉ ህዝብም በዕውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለግድቡ ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ በተከናወነው የድጋፍ ማስተባበር ስራ 10 ሚሊዮን ብር  ገቢ መሰብሰቡን አክለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም የክልሉን ህብረተሰብ በማሳተፍ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ ሄኖክ አስታውቀዋል።

በክልሉ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል የተያዘው እቅድ ስኬታማ እንዲሆን ከክልል ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎች የውይይት እና የህዝብ ንቅናቄ መድረክ የመፍጠር ስራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም