አርሶአደሮች በአፕል ልማት ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ጥሪት ማፍራት ጀምረዋል

አርባ ምንጭ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦የአፕል ልማት ሥራቸው ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ኑሯቸውን ለማሻሻልና ጥሪት ለማፍራት እንዳስቻላቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አፕል አምራቾች በአፕል ልማት መሰማራታቸውን ተከትሎ ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።  

የጨንቻ ከተማ ነዋሪ አቶ ማቴዎስ በቀለ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የመንግስት ሥራ ለቀው ወደ አፕል ልማት ከተሰማሩ በኋላ በህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያዩ መምጣታቸውን ገልጸዋል።


 

በአንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ከ200 ሺህ በላይ የአፕል ችግኞችን በማፍላት ለተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም አርሶ አደሮች በመሸጥ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል። 

"ህይወቴ እንዲለወጥ የአፕል ልማት መሰረት ሆኖኛል" ያሉት አቶ ማቴዎስ፣ ከአፕል ሽያጭ ገቢ አንድ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በመግዛት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመፍጠር ባለፈ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በጨንቻ ከተማ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚውሉ ተቋማትን በመክፈት ለእንግዶችና ለአካባቢው ማህበረሰብ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በየዓመቱ ከአፕል ችግኝ ሽያጭ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያገኙ የጠቀሱት አቶ ማቲዎስ፣ በቀጣይ ልማቱን በማስፋት ለሀገር አቀፍና አህጉራዊ ገበያዎች ለማቅረብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

በጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የዳሎና ዛራ ቀበሌ አርሶ አደር መለሰ መርዕድ በበኩላቸው እንዳሉት በአፕል ምርት ሽያጭ ኑሯቸውን ማሻሻል ከመቻላቸው በላይ ሁለት ልጆቻቸውን አስተምረው ለማዕረግ አብቅተዋል።


 

አፕል ምርታማና በገበያ ተፈላጊ መሆኑን ጠቁመው በልማቱ ምርታማ እንዲሆኑ የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የጨንቻ አካባቢ ነዋሪዎች በእንሰት፣ ገብስ፣ ስንዴ እና ድንች ልማት ሲተዳደሩ እንደነበረና አሁን ግን አፕል ዋነኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የዶርዜ ጉድቆ ቀበሌ አርሶ አደር እሸቱ ማናዬ ናቸው።

የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ህብረት ሥራ ጽህፈት ቤት የማህበራት ማስፋፊያና ማደራጃ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታደሰ ዘውዴ አርሶ አደሮች ከአፕል ልማት ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ በዘርፉ ከተሰማሩ ሰባት ማህበራት ጋር እንዲተሳሰሩ መደረጉን ገልጸዋል።

የአፕል ልማት በአጭር ጊዜ የህብረተሰቡን ህይወት እየቀየረ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ ልማቱ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ እንዲታገዝ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

የአፕል ተክል ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ለውጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ደረጀ ሙሉ ናቸው።


 

"የግብርናውን ዘርፍ በማነቃቃት ብዙዎችን ከድህነት ያላቀቀና ለአካባቢው ማህበረሰብም ባለውለታ ተክል ነው" ብለዋል።

በወረዳው ሁሉም ቀበሌዎች የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ለአምራቾች አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቁመዋል። 

የወረዳው ነዋሪዎች አፕል በማምረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ ችግኝ የማባዛትና የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም