በዓላትን እና የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ አስመልክቶ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦ በዓላትን እና የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪን አስመልክቶ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የአቅርቦትና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለፁ። 

ህብረተሰቡ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ መረጃ መስጠት እንደሚገባውም ጠቁመዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገበያ ማረጋጋት፣ ህገወጥ ንግድ ቁጥጥርና የኢትዮጵያ-አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ግብረ ኃይል የዘመን መለወጫ የበዓል ገበያን አስመልክቶ እና ከዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም በከተማዋ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያን ለማረጋጋት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል። 

አቅርቦትን ለማስፋት የሚያስችሉ 219 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መኖራቸውን ገልፀው፤ አምስት የገበያ ማዕከላት በከተማ ደረጃ ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ግብረ-ሀይሉ ገበያን በማረጋጋት እና ህገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ህብረተሰቡ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዓላትንና የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪን አስመልክቶ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የአቅርቦትና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። 

ህብረተሰቡ የህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ላይ መረጃ መስጠት ይገባዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም