አሌክሳንዳር አይዛክ ዋና አጀንዳ የሆነበት የኒውካስትል ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
አሌክሳንዳር አይዛክ ዋና አጀንዳ የሆነበት የኒውካስትል ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2017(ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በኒውካስትል ዩናይትድ እና ሊቨርፑል መካከል ይካሄዳል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከምሽቱ 4 ሰዓት በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም ይካሄዳል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በመጀመሪያው ጨዋታ ቦርንማውዝን 4 ለ 2 አሸንፏል።
ኒውካስትል ዩናይትድ ከአስቶንቪላ ጋር ባደረገውየመጀመሪያ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይቷል።
ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች 190 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሊቨርፑል 94 ጊዜ ሲያሸንፍ ኒውካስትል ዩናይትድ 51 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 45 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 56 ጨዋታዎች አድርገው ሊቨርፑል 35 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ኒውካስትል ዩናይትድ 9 ጊዜ ድል ሲቀናው 12 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።
ከሁለቱ ቡድኖች የሰኞ የሜዳ ላይ ጨዋታ ይልቅ የበለጠ ትኩረትን የሳበው ስዊድናዊው የኒውካስትል ዩናይትድ አጥቂ አሌክሳንደር አይዛክ ጉዳይ ነው።
ኒውካስትል ዩናይትድ ከሊቨርፑል አይዛክ ለመግዛት ያቀረበው የ110 ሚሊዮን ፓውንድ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ተጫዋቹ ለክለቡ ለመጫወት እንደማይፈልግና ወደ ሊቨርፑል ማምራት እንደሚፈልግ ገልጿል።
አይዛክ ከቡድኑ ጋር ልምምድ እየሰራ የማይገኝ ሲሆን ከአስቶንቪላ ጋር በነበረው ጨዋታም አልተሰለፈም። በዛሬውም ጨዋታ አይሰለፍም።
ስዊድናዊው አጥቂ በሳምንቱ አጋማሽ በተደረገው የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር (PFA) ሽልማት ስነ ስርዓት አስመልክቶ በኢንስታግራም ገጹ ላይ የሰጠው አስተያየት መነጋገሪያ ሆኗል።
ተጫዋቹ በሰጠው አስተያየት ኒውካስትል ዩናይትድን መልቀቅ የረጅም ጊዜ አቋሜ እንደሆነ ክለቡ ያውቃል፤ በክለቡ መቀጠል አልፈልግም ሲል ገልጿል።
ክለቡ የአይዛክን አስተያየት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በተጫዋቹ ንግግር ቅር መሰኘቱን አስታውቋል።
አሌክሳንደር ኢሳክ ከእኛ ጋር ኮንትራት እንዳለው እና በክረምቱ ኒውካስትል ዩናይትድን ሊለቅ እንደሚችል በክለቡ ባለስልጣናት ምንም አይነት ውሳኔ እንዳልተሰጠ አመልክቷል።
መግለጫዎቹን ተከትሎ አይዛክ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ክለቡን ሊለቅ እንደማይችል እየወጡ ያሉ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ተጫዋቹ ለኒውካስትል ዳግም ይጫወታል ተብሎ አይጠበቅም። የኒውካስትል ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤዲ ሃው፣ ዳን በርን እና አንቶኒ ጎርደን የኢዛክ ጉዳይ በአፋጣኝ እልባት እንዲያገኝ ጠይቀዋል።
ጉዳዩ በኒውካስትል ዩናይትድ የቡድን መንፈስ ላይ መረበሽ መፍጠሩ እየተገለጸ ይገኛል ምንም እንኳን ጎርደን ቡድኑ በጥሩ ስሜት ላይ እንደሚገኝ ቢናገርም።
የ43ኛ ዓመቱ እንግሊዛዊ ሳይመን ሁፐር የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።