ፉልሃም እና ማንችስተር ዩናይትድ ነጥብ ተጋርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ፉልሃም እና ማንችስተር ዩናይትድ ነጥብ ተጋርተዋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ፋልሃም እና ማንችስተር ዩናይትድ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ማምሻውን በክራቫን ኮቴጅ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የፉልሃሙ አጥቂ ሮድሪጎ ሙኒዝ በ58ኛው ደቂቃ በራሱ መረብ ላይ ባስቆጠረው ግብ ማንችስተር ዩናይትድ መሪ ሆኖ ነበር።
ተቀይሮ የገባው የአርሰናል የቀድሞ ኤሚል ስሚዝ ሮው በ73ኛው ደቂቃ ፉልሃምን አቻ ያደረገችውን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
የማንችስተር ዩናይትድ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ በ38ኛው ደቂቃ ቡድኑ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ስቷል።
በጨዋታው ፉልሃም በኳስ ቁጥጥር እና ግልጽ የግብ እድሎችን በመፍጠር የተሻለ ነበር።
ውጤቱን ተከትሎ ፉልሃም በሁለት ነጥብ 13ኛ፣ ማንችስተር ዩናይትድ በአንድ ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዘዋል።
በሶስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ፉልሃም ከቼልሲ፣ ማንችስተር ዩናይትድ ከበርንሌይ ይጫወታሉ።
በተያያዘም ዛሬ በተደረጉ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኤቨርተን ብራይተንን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ክሪስታል ፓላስ ከኖቲንግሃም ፎረስት አንድ አንድ አቻ ተለያይተዋል።