ቀጥታ፡

ህብረት ስራ ማህበራት ገበያን በማረጋጋትና የስራ ዕድል በመፍጠር የጎላ ሚና እየተጫወቱ ነው

ድሬዳዋ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡- ህብረት ስራ ማህበራት ገበያን በማረጋጋትና የስራ ዕድል በመፍጠር በማህበራዊ እና በምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የጎላ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ገለፀ።

በድሬዳዋ የሚገኘው "የኛ የገንዘብ ቁጠባ ህብረት ስራ ማህበር 2ተኛ አመታዊ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል ።

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን የፋይናንስ ህብረት ስራ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ዱፌራ  በወቅቱ እንደገለጹት  የህብረት ስራ ማህበራት የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋት አበረታችና ውጤታማ ስራዎች እያከናወኑ ነው።

ገበያን በማረጋጋትና የስራ ዕድል በመፍጠር በማህበራዊና በምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የጎላ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የግብርና ግብአቶችንና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የግብርና ልማት ወደ ላቀ እምርታ እንዲሸጋገር በማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

 የአርሶና አርብቶአደሩን ምርቶች ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት በማቅረብ ገበያን በማረጋጋትና ምንዛሬን በማስገኘት  አበረታች ስራዎች እያከናወኑ መሆኑንም አመልክተዋል።

የገንዘብና ቁጠባ ማህበራትም የቁጠባ ባህልን በማስፋት የፋይናንስ ተደራሽነት በማሳደግ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በገቢ ማግኛ ስራዎች እንዲሰማሩ በማድረግ የሚያከናውኗቸው ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል ።

የሁለተኛውን አመት ጠቅላላ ጉባኤ ያካሄደው የድሬዳዋ "የኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር"  የስራ አጥነትንና የፋይናንስ አቅርቦት  ችግሮችን ለመፍታት የጀመራቸው ስራዎች  በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን አንስተዋል።

ማህበሩ በሁለት አመት ዕድሜው ለ20 ወጣቶች የታክሲ ተሽከርካሪዎች በማቅረብና አባላቱን የቤት ባለቤት ለማድረግ የጀመራቸውን ስራዎችን አድንቀው ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ማህበር በአስተዳደሩ ከተመሠረቱ እና ተልዕኳቸውን በትክክል እየተወጡ ከሚገኙት ማህበራት ግንባር ቀደም መሆኑን የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ፣ማደራጃና  ግብአት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አሜ ናቸው።

ማህበሩ በቁጠባ፣ በብድር፣ የስራ ዕድል ፈጠራና ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል   የሚያከናውናቸውን ስራዎች ሌሎች ማህበራት በተሞክሮ እንዲያስፋፉ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ስራ ማህበር ምክትል ሊቀ-መንበር ወይዘሮ ትዕግስት አለማየሁ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት አመት ሶስት ሺ ከሚጠጉ አባላት ከመደበኛ ቁጠባ  ከ82 ሚሊዮን 700ሺ ብር በላይ ቁጠባ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ማህበሩ  በተጠናቀቀው በጀት አመት  7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ጠቅሰው ማህበሩ በዘንድሮ በጀት አመት አደረጃጀትና አሰራሮቹን በማዘመንና አባላቱን በማሳደግ  ውጤታማነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም