በሀገር ግንባታ ላይ የወጣቶችን አስተዋጽኦ ለማጎልበት የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ግንባታ ላይ የወጣቶችን አስተዋጽኦ ለማጎልበት የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-በሀገር ግንባታ ላይ የወጣቶችን አስተዋጽኦ ለማጎልበት የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
የዓለም ዓቀፍ የወጣቶች ቀን "የተደመረ የወጣቶች አቅም ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት" በሚል መሪ ሀሳብ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶች የወጣት አደረጃጀቶች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተገኙበት ተከብሯል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተሰፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የፖሊሲ ዝግጅቶች፣ የአደረጃጀት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የስራ ፈጠራ ስራዎች፣ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት፣ ወጣት ተኮር የጤና አገልግሎቶችና ሌሎች በርካታ ስራዎችን ጠቅሰዋል።
ወጣቶች በኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ፖለቲካ ዘርፎችም ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ወጣቶች በሀገር ግንባታ ስራዎች ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የወጣቶች ስብዕና ማዕከላትን ለማጠናከር እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሚያበረክቱትን ሚና ለማጎልበት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ወጣቶች በተደመረ አቅም በመንቀሳቀስ ለኢትዮጵያ ብልጽግና የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የአጋር አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ማደግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና በበኩሉ፤ የወጣቶችን ቀን የምናከብረው ለመገንባት የምንመኛትን ኢትዮጵያ በተደመረ የወጣቶች አቅም እውን ለማድረግ በማለም ጭምር ነው ብሏል።
ምክር ቤቱ ወጣቶች እጣ ፈንታቸውን ከወዲሁ በራሳቸው ጥረት የሚገነቡና ለትውልድ የሚያወርሱትን እርሾ መፍጠር የሚችሉ፤ የነቃና የበቃ ትውልድ መፍጠርን አልሞ የተቋቋመ አደረጃጀት ነው ብሏል።
በዩዝ ኔትወርክ ፎር ሰስተነብል ዴቨሎፕመንት ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ አለማየሁ የወጣቶችን አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን በአካባቢ ጥበቃ፣ ጤና፣ ሰብአዊነትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢንጀንደርድ ሄልዝ የተሰኘ አለም አቀፍ ድርጅትን በመወከል የተገኙት አቶ ብሩክ ማሞ ድርጅቱ የወጣቶችን ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማጎልበት የሚያከናውናቸው ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።