ለዕቅዱ ስኬታማነት አመራሩ በትጋትና በጥበብ መስራት አለበት-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህር ዳር ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-የክልሉን የአምስት ዓመት አሻጋሪ ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ አመራሩ ጠንካራ የልማት ትግል ማድረግ እና  በትጋትና በጥበብ መስራት እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።

"አርቆ ማየት፤ አልቆ መስራት ለህዝባችን ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ እንዲሁም የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ያተኮረ ውይይት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋ ከበደ በመድረኩ እንደገለጹት፣ ስትራቴጂክ ዕቅዱ በክልሉ ያለውን ፀጋ በመጠቀም የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነትና የክልሉን እድገት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።

ክልሉ አሁን ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ በጥልቀት ከማመላከት ባለፈ በክልሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰላም ጉዳዮች ላይ  የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት መሆኑን አመልክተዋል። 

ዕቅዱ በትውልዶች ቅብብል የሚተገበር ነው ያሉት አቶ አረጋ፣ ቀጣይና ተከታታይ በሆነ መንገድ ተደማሪ ውጤት በሚያስመዘግብ አግባብ የሚተገበር መሆኑንም አስረድተዋል።

በተለይ በዚህ ዓመት የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት የይቻላል መንፈስን በሚፈጥር መንገድ መተግበር ዋነኛ ትኩረታችን መሆን አለበት ሲሉም ነው ያሳሰቡት።

በዕቅዱ ላይ ህዝብን በባለቤትነት ለማሳተፍ ውይይት መደረጉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በዚህም ህዝቡ ተስፋ ማድረጉንና ተስፋውን እውን ለማድረግ አመራሩ በቁጭትና በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ችግር ቀልባሽና አሻጋሪ ሆኖ የተዘጋጀውን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ እምቅ የአመራር ጥበብን መጠቀምና በጥበብና በትጋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለዚህም አመራሩ ከልማዳዊ አሰራር ወጥቶ ሥራውን በላቀ ትጋት በማከናወን የህዝብን የልማት እርካታ ማረጋገጥ አለበት ሲሉም ነው ያስገነዘቡት።

የበለፀገ ህዝብና ክልል ለመገንባት ከተናጠል ጥረት ይልቅ የጋራ ትጋት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ሀላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) ናቸው።


 

የክልሉ የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ እንዲሁም የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን በሚያሳካ አግባብ ተነድፎ ወደ ትግበራ መገባቱን አንስተዋል።

ዕቅዱ የህዝብ መሆኑን ጠቁመው፣ አመራሩ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት በላቀ ቁርጠኝነትና መግባባት እውን ሊያደርገው እንደሚገባ ገልፀዋል።

መድረኩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አመራሮችም በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም