“ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” መጽሀፍ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ቁልፍ ሚና ሊጫወት ይችላል - ኢዜአ አማርኛ
“ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” መጽሀፍ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ቁልፍ ሚና ሊጫወት ይችላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-“ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” በሚል ርዕስ ለሕትመት የበቃው የተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) መጽሀፍ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ ቁልፍ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ተገለጸ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ተጽፎ ለአንባብያን የደረሰው መጽሀፍ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
መጽሀፉን በተመለከተ በተለያዩ የስራ መስኮች የሚገኙ ባለሙያዎች እና ባለስልጣናት ውይይት አድርገውበታል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ባወያዩት መድረክ መጽሀፉ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ በስፋት ተዳሷል፡፡
በመድረኩ ላይ ሀሳባቸውን ያካፈሉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በመጽሀፉ ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ግንባታ እርሾ የሚሆን የዳበረ ማህበራዊ እና አስተዳደራዊ እሴት አላት።
ሌላው በውይይቱ የተሳተፉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ በሰጡት አስተያየት ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሲነሳ ከሀገረ መንግስቱ ጋር ተጣምሮ የሚነሳ በመሆኑ የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞውን እንዳወሳሰበው ገልጸዋል፡፡
መጽሀፉ ይህን የዘመናት የዴሞክራሲ ጥያቄ ከኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ጋር አገናኝቶ ማምጣቱ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን የመሰለ ጥንታዊት እና የዳበረ ባህላዊ ስርዓት ያላተ ሀገር ዴሞክራሲን መገንባት እንቆቅልሽ ያደረገው ምስጢር እንቅልፍ እንደሚነሳቸው የተናገሩት ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር)፤ ይህ ቁጭት “ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ፍለጋ” የሚለውን መጽሀፍ እንዲጽፉ እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡
መጽሀፋ ወደፊት ለኢትዮጵያ የሚበጅ ዴሞክራሲን በመገንባት ሂደት መነሻ ሀሳብ ሆኖ እንደሚያገለግል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡