በምግብ ራስን ለመቻልና ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ በተጀመሩ ተግባራት አበረታች ለውጥ እየተመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምግብ ራስን ለመቻልና ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ በተጀመሩ ተግባራት አበረታች ለውጥ እየተመዘገበ ነው
አዳማ ፤ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡- በምግብ ራስን ለመቻልና ስርአተ ምግብን ለማረጋገጥ በተጀመሩ ተግባራት አበረታች ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የአብይ ኮሚቴ የምክክር መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን እንደገለፁት ግብርናውን ለማሻገርና ለማዘመን እየተደረገ ያለው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው።
በምግብ ራስን ለመቻልና ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ የተለያዩ ኢንሼቲቮች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ያሉት ዶክተር መለስ በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በስንዴ፣ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ፣ በሌማት ትሩፋት ፕሮግራም፣ በመካናይዜሽን ማስፋፋትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በመንደፍ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል ።
በተለይ በመኸርና የበጋ መስኖ ስንዴና በሩዝ ልማት ፣ በወተት ላሞች ዝርያ ማሻሻያና በማር ልማት ጨምሮ በሌማት ትሩፋት የአርሶአደሩን ህይወት እየቀየሩ ያሉ ተስፋ ሰጪ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል ።
የዝናብ ጥገኛ የነበረውን የግብርና ዘርፍ በመስኖና ቴክኖሎጂ በመደገፍ ዘርፉን ለማሻገርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጅምር ስራዎች ውጤት እየተገኘባቸው መሆኑን አመልክተዋል።
የተበጣጠሰ የአርሶአደሩን መሬት በኩታ ገጠም በዋና ዋና ሰብሎች በማልማት ምርትና ምርታማነትን የጨመርንበትን ሂደት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አስታውቀዋል።
በሚኒስቴሩ የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማኔጀር አቶ ከበሩ በላይነህ በበኩላቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ ትግበራ ለአርሶአደሩ የኤክስቴንሽንና አዳዲስ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ማድረግ ፣ የመስኖ ውሃ ተጠቃሚ ማህበራትን ማደራጀት ፣ የሰብልና የወተት ሀብት የገበያ ማዕከላትን መገንባት እንዲሁም በመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል ።
በተያዘው የበጀት ዓመት በፕሮጀክቱ ሁሉም መስኮችና ኢንሼቲቮች የተያዙ እቅዶችን ለማሳካት መድረኩ ቀጣይ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑን አስታውቀዋል።
በመድረኩ የፌዴራልና የክልሎች የግብርና ሴክተር አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።