የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን ተቀብሎ ምርመራ ያካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን ተቀብሎ ምርመራ ያካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-ዜጎች በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ የአስተዳደር በደል አቤቱታዎችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በማቅረብ ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ እንደሚችሉ የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኢፌዲሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 15 መሰረት በአዋጅ ቁጥር 211/1992 የተቋቋመ ህገ መንግስታዊ የዲሞክራሲ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1142//2011 መሰረት አስተዳደራዊ በደልን አስቀድሞ መከላከል እና ተፈጽሞ ሲገኝ በፍጥነት እንዲታረም ለማድረግ የተቋቋመ ነው፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1142//2011ን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1307/2016 መሰረት በግል ድርጅቶች የሚፈጸሙ አሰተዳደራዊ በደሎችን ተቀብሎ የመመርመር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስተዳደራዊ በድሎችን በመመርመር የመፍትሔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡
በአስፈፃሚ ተቋማት ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን የመመርመር፣ ጥናት የማድረግ፣ ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነት ያለበት ነፃና ገለልተኛ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከቀረቡለት ከሁለት ሺህ በላይ አቤቱታዎች ከ900 በላይ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ አቤቱታዎች ከይዞታ፣ ጡረታ፣ ከአሰሪና ሰራተኛ እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የቀርቡ አቤቱታዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የገለጹት ዋና ዕንባ ጠባቂዋ፤ የዜጎችን ቅሬታ በፍጥነት ዕልባት መስጠት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠበቂ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 1307/2016 መሰረት ኢትዮጵያ ከደረሰችበት ዕድገት አንጻር በግል ድርጅቶች የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን አቤቱታ ተቀብሎ ምርመራ የማካሄድ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በዚህም የግል ድርጅት ሰራተኞች በግል ድርጅቶች የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን ለዕንባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታዎችን ማቅረብ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ዜጎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገቢ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ብለው ቅሬታ ማቅረብ እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ዕንባ ጠባቂዋ፤ ተቋሙ በፍርድ ቤት የተያዙና ከጸጥታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማየት ኃላፊነት አልተሰጠውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚቀርቡለትን አስተዳደራዊ ችግሮች ያለምንም ክፍያ በፍጥነት ዕልባት እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ዜጎች የተቋሙን ኃላፊነት በውል ተረድተው እንዲገለገሉበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡