ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ 550 ሺህ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር ተገብቷል

አዳማ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-በተያዘው በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 550 ሺህ ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደተግባር መገባቱን የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ የመጀመሪያ 45 ቀናት የክረምት ወቅት ደም ማሰባሰብ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ በአዳማ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት እንደ ሀገር በቂና ጥራቱን የጠበቀ ደም ለጤና ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። 

በመሆኑም የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ደም የመሰብሰብ፣ የመመርመር፣ የማከማቸትና ለህክምና ተቋማት የማሠራጨት ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። 

እንደ ሀገር በቂ የደም አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግና የደም ህክምና የሚፈልጉ ታካሚዎችን ህይወት ለመታደግ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በደም ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላትም ወጣቶችን፣ ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በባለቤትነት በማሳተፍ በተሰራው ሥራ መሻሻል መታየቱን ጠቅሰዋል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከበጎ ፈቃደኞች 90 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በ45 ቀናት ውስጥ ብቻ 60 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

በዓመቱ ለመሰብሰብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች በየአካባቢው ለደም ልገሳ ተብለው በተዘጋጁ የደም ባንኮችና ተንቀሳቃሽ ጣቢያዎች ደም እንዲለግሱም ጥሪ አቅርበዋል።

በአገልግሎቱ የደም ለጋሾች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር መላሽ ገላው በበኩላቸው ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ አንድ በመቶ የሚሆነው ደም መለገስ ቢኖርበትም እየለገሰ ያለው ከዜሮ ነጥብ አራት በመቶ በታች ነው ብለዋል።


 

ይህንን ለማሳደግ ህብረተሰቡ በሰብአዊ መርህ ተመስርቶ የበጎ ፈቃድ ደም እና የዓይን ብሌን ልገሳውን እንዲያጠናክር በአገልግሎቱ በኩል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት እንደ ሀገር ከበጎ ፈቃደኞች 513 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሠብ ታቅዶ 423 ሺህ 295 ዩኒት ደም መሰብሰቡን አስታውሰው፣ ይህም ከሕክምና ተቋማት ፍላጎት አንጻር ሲታይ በቂ አይደለም ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም 550 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን ዶክተር መላሽ  አመላክተዋል።

በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ ለ45 ቀናት ከበጎ ፈቃደኞች በአደባባዮች ደም የማሰባሰብ ሥራ መከናወኑን ገልጸው፣ በቀጣይም በተቋማትና በአደባባይ ደም የማሰባሰብ ሥራው ይጠናከራል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ለ45 ቀናት በተካሄደው ንቅናቄ 16 ሺህ 837 ዩኒት ደም መሰብሰቡን የጠቆሙት ዶክተር መላሽ፣ አፈጻጸሙም የዕቅዱ 84 በመቶ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ለጋሾች ማህበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ የደም ልገሳ አስተባባሪ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም