የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ያረጋገጠ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እየተሰራ ነው - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ያረጋገጠ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እየተሰራ ነው - ኮሚሽኑ
ደሴ ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-የአካል ጉዳተኞችን መብት፣ ጥቅም እና ተሳትፎን ያረጋገጠ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ገለፁ።
ኮሚሽኑ "የአካል ጉዳተኞች ሚና እና አስተዋጽኦ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሀሳብ ከአካል ጉዳተኞች ጋር በደሴ ከተማ መክሯል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያማከለ አካታችና አሳታፊ ምክክር በማካሄድ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እየተሰራ ነው።
በተለይም የአካል ጉዳተኞችንና ሌሎች ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን መብት፣ ጥቅምና ተሳትፎ ያካተተ ምክክር ለማድረግ የሚያስችሉ አጀንዳዎችና ተሳታፊዎች ተለይተዋል ብለዋል።
በዚህም ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጀምሮ የሚስተዋሉ ጥያቄዎች፣ ስጋቶችና ሌሎች ችግሮች መልስ እንዲያገኙ ሁሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
አካል ጉዳተኞችም አጀንዳዎችን በማስያዝ፣ ምክረ ሀሳብ በመስጠት፣ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በመደገፍና ለሌሎችም ግንዛቤን በመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የፕላንና ፕሮግራም ማኔጀር አቶ ስለሺ ተመስገን በበኩላቸው በምክክሩ አካል ጉዳተኞች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም አካል ጉዳተኞች የፖለቲካ ውክልናና ተሳትፎ እንዲሁም ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው፣ ፖሊሲዎችና የህግ አሰራሮች እንዲሻሻሉ አጀንዳዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።
ከኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ኑሩ አያሌው በበኩላቸው ምክክሩ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አጀንዳዎች መሰባሰባቸውን ተረድቻለሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ፣ ተፈጥሮ ያደላት የሁላችንም ሀገር በመሆኗ የሁላችንም ሀሳብ በምክክሩ ተካቶ ችግሮቻችን መፍትሔ እንዲያገኙ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ አካታችና አሳታፊ ምክክር በማካሄድ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሀገር ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ ከሰሜን ወሎ ዞን የመጡት ተሳታፊ ወይዘሮ ሙሉ ተጋፈው ናቸው።
ዛሬ በተካሄደው ውይይትም የሀገራዊ ምክክሩን ጠቀሜታ፣ ሀሳብና ዓላማ መረዳታቸውን ጠቁመው ለውጤታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በውይይቱ ከደቡብ ወሎ ዞንና አጎራባች የክልሉ ዞኖች እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፈዋል።