አፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት በትብብር ይሰራሉ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት በትብብር ይሰራሉ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 18 /2017 (ኢዜአ)፦አፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት በትብብር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
ዘጠነኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም(ቲካድ) በዮካሃማ መካሄዱን ቀጥሏል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ፕሬዝዳንት አኪሂኮ ታናካ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር የጃይካ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንዲሁም ኢኮኖሚና ማህበራዊን ጨምሮ በአፍሪካ ቁልፍ ዘርፎች እያደረገ ያለውን ኢንቨስትመንት አድንቀዋል።
ሊቀ መንበሩ እና ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ህብረት እና ጃፓን ያላቸውን የጋራ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዘጠነኛውን የቲካድ ፎረም መንፈስ ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ለውጥ በጋራ የመፍጠር ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባም አንስተዋል።
ከነሐሴ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ፎረም የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።