የውሃ እና ተያያዠ የናሙና ምርመራ ማድረግ የሚያስችል ስፔሻላይዝድ ላብራቶሪ በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የውሃ እና ተያያዠ የናሙና ምርመራ ማድረግ የሚያስችል ስፔሻላይዝድ ላብራቶሪ በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-ስድስት አይነት የውሃ እና ተያያዠ ናሙና ምርመራ ማድረግ የሚያስችል ስፔሻላይዝድ ላብራቶሪ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትየጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ስፔሻላይዝድ ላብራቶሪ መሪ ስራ አስፈጻሚ አብዱራሀማን ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ተቋማት በሚቀርቡለት የውሃ ናሙናዎች ላይ ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ይፋ ያደርጋል፡፡
ኢንስቲትዩት በማይክሮ ባይሎጂካልና በፊዚኮ ኬሚካል ዘርፍ የምርመራ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በፊዚኮ ኬሚካል ላቦራቶሪ በውሃ ውስጥ ያሉ ኬሚካሎችን መጠን በመለካት ውሃው ለሚፈለገው አገልግሎት መዋል የሚችል መሆኑን የማረጋገጥ ምርመራ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
እንዲሁም በማይክሮባዮሎጂ ላቦራቶሪ በውሃ ውስጥ ያሉ በሽታ አምጪ ተዋህስያንን መለየትና መተንተን የሚያስችል ምርመራ እንደሚያከናውን ነው ያስረዱት።
ኢንስቲትዩቱ ዘመናዊ ስፔሻላይዝድ ላብራቶሪ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ስድስት አይነት የውሃ ምርመራ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ የአካባቢና የህዝብን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ቶክሲኮሎጂ የውሃ ምርመራ እንዲሁም ለውሃ ሀብት አስተዳደር ጠቃሚ መረጃ የሚሰጠውን የአኳቲክ ባዮሎጂ ምርመራ የሚሰጥ እንደሚሆን ተናግረዋል።
እንዲሁም የአፈርና የድንጋይ ፊዚካል እና ሜካኒካል ባህሪዎችን በማጥናት በመጠጥ ውሃ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅእኖ ለመረዳት የሚያስችል ጂኦቴክኒካል ምርመራ በቅርቡ መስጠት የሚጀመር መሆኑን አስታውቀዋል።
የተጀመሩ ስራዎች በዋነኝነት ኢትዮጵያ ለውሃ ምርመራ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ነው የገለፁት።