ቀጥታ፡

ከኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18/2017(ኢዜአ)፡-ከኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታውቋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ከኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

አሁንም በተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች እጅ የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ የት ቦታ እና ማን ጋር ምን አይነት ቅርስ ይገኛል የሚለውን የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ከሀገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ለተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንደማስረጃ የሚቀርበው ተለይቶ የተሰነደ ማስረጃ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረገ ጥረት በርካታ ቅርሶችን ማስመለስ መቻሉን አንስተዋል።

በተለያዩ ግለሰቦች እጅ የሚገኙ ቅርሶችን በፈቃደኝነትና በድርድር ማስመለስ መቻሉ ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቅርሶች በተለያዩ የዓለም ሀገራት ለጨረታ ሲቀርቡ በህጋዊ መንገድ ከጨረታ እንዲወርዱ በማድረግ ለማስመለስ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት አመት የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ፣ የራስ ደስታ ዳምጠው ካባ፣የኢትዮጵያ ኮከብ ኒሻን እና ሌሎች ከጨረታው እንዲወርዱ በማድረግ ማስመለስ መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።

በቅርስ ማስመለስ ስራ ላይ የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፥ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ አዳዲስና ወካይ የሆኑ የተፈጥሮ እና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም አልነጃሺን፣ ቡናን፣ ዋዛ(በተለምዶ ዙምባራ የሚባለው)፣ አገው ፈረሰኛ፣ ሀላባ ሴራ፣ እንሰት እና መሰል ቅርሶችን ማስመዝገብ የሚያስችል የሰነድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በቀጣይም ብሔራዊ እና የወል የሆኑ የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም