የወታደር ውሎ አዳር መጽሐፍ መጪው ትውልድ የሠራዊቱን ጀግንነት በውል እንዲረዳ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የወታደር ውሎ አዳር መጽሐፍ መጪው ትውልድ የሠራዊቱን ጀግንነት በውል እንዲረዳ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፡- የወታደር ውሎ አዳር መጽሐፍ መጪው ትውልድ የሠራዊቱን ጀግንነት በውል እንዲረዳ የሚያደርግ መሆኑን የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ ገለጹ፡፡
በሌተናል ኮሎኔል ፈይሳ ናኔቻ የተጻፈው "የወታደር ውሎ አዳር" የተሰኘው መጽሐፍ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተመርቋል።
በ23 ምዕራፎች የተከፋፈለው ይህ መፅሐፍ ለሠራዊት የስነ-ልቦና ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ጥጋቡ ይልማ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የወታደር ውሎ አዳር መጽሐፍ ሠራዊቱ ከማሰልጠኛ ጀምሮ ያለውን እውነተኛ ህይወት የሚያስቃኝ ነው ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ በደሙ የሚያስጠብቀውን የሀገር ሉዓላዊነትና የሚፈጽማቸውን ጀብዶች ሰንዶ ለመጪው ትውልድ ከማስተላለፍ አንጻር ደራሲው ስኬታማ ስራ መስራቱን ተናግረዋል፡፡
መጪው ትውልድ መሰል መጽሐፎችን በማንበብና ታሪክን በመረዳት የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ይበልጥ ማጽናት እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል፡፡
የወታደር ውሎ አዳር መጽሐፍ ደራሲ ሌተናል ኮሎኔል ፈይሳ ናኔቻ፥ መጽሐፉ የሠራዊቱን ህይወት የሚያስቃኝና ጥንካሬውን የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለሠራዊቱ የስነ-ልቦና ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ጠቁመው ሠራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የሞራል ስንቅ እንደሚሆነውም አንስተዋል፡፡
በመከላከያ የስነልቦና ግንባታ ዋና መምሪያ የሚዲያ ሥራዎች ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል አስፋው ማመጫ፤ የወታደር ውሎ አዳር መጽሐፍ የሠራዊቱን እውነተኛ መልክ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ደራሲው በመጽሐፉ ሀገርን መውደድና ማክበርን በጉልህ ያስቃኘ መሆኑን ጠቁመው ሠራዊቱ ያሳለፈውን የውትድርና ህይወት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመጽሐፉ ምረቃ ላይ የተገኙት ሻለቃ አስቻለው ኛኙኬ እና ሻለቃ ስንታየሁ ለማ፤ መፅሐፉ ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና የህዝብን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ የሚከፍለውን የጀግንነት ዋጋ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ከሠራዊት ግንባታ አንጻር የሚሰጠው ጠቀሜታም ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመፅሐፉ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ጀነራል መኮንኖች፣ የሠራዊቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሠራዊት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።