ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትውልዱ ጥንካሬና የህብረ ብሄራዊ አንድነት ሁነኛ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትውልዱ ጥንካሬና የህብረ ብሄራዊ አንድነት ሁነኛ ማሳያ ነው
አምቦ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ) :- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትውልዱ ጥንካሬና የህብረ ብሄራዊ አንድነት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን የምዕራብ ሸዋ ዞን እና የአምቦ ከተማ ፖሊስ አባላት ተናገሩ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ነቀምቴ ከተማ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ አምቦ ከተማ ሲገባ አቀባበል ተደርጎለታል።
ዋንጫው አምቦ ከተማ ሲገባም የዞኑና የከተማው ፖሊስ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች፣ እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በስፍራው በመገኘት አቀባበል አድርገዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የምዕራብ ሸዋ ፖሊስ ጽፈት ቤት ኃላፊ ኮሚሽነር ሁንዴ በቀሌ፤ የፖሊስ አባላት ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ለህዳሴው ግድብ የቦንድ ግዥና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፍና እገዛዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ የትውልዱ የጥንካሬና የህብረ ብሄራዊ አንድነት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አንስተው የፖሊስ አባላቱ እገዛና ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በአምቦ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የእቅድና በጀት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ከበደ ገላልቻ፤ የፖሊስ አባላት ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍ ከጅምሩ እስካሁንም ድረስ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
የግድቡ ግንባታ የእዚህ ትውልድ የጥንካሬ መገለጫ እና የህብረ ብሄራዊ አንድነት ማሳያ መሆኑን አንስተው መሰል ስኬቶችን ለማስመዝገብ የጋራ ጥረታችን መቀጠል አለበት ብለዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከተገኙት የምዕራብ ሸዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ጉደታ ድሪባ፤ የግድቡ ግንባታ ስኬት በቀጣይ ለሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ስራዎችም በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ በመቀበል ለህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ ለዞኖችና ከተሞች የጸጥታ ዘርፍ አባላት ማስረከቡ ይታወሳል።
በዚሁ ጊዜ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ፤ የፀጥታ ሀይሉ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ የህዳሴ ግድብ ከፍጻሜው እንዲደርስ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።