በክልሉ ተኪ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የማስፋት ስራዎች ተጠናከረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ተኪ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የማስፋት ስራዎች ተጠናከረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ተኪ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የማስፋት ስራዎች ተጠናከረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
በሲዳማ ክልል “የኢትዮጵያን ይግዙ” የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛር መጀመሩን አስመልከቶ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ ተኪ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች እየተጠናከሩ እንዲሄዱ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመግዛት ዝንባሌ ማደግ እንዳለበት አመልክተዋል።
በሲደማ ክልል የሀገር ውስጥ ምርትን በስፋት ለማምረት ብሎም ግብይቱን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት የሚጠናከር መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑን ጠቅሰው በእንስሳት እና በእርሻ ልማትም ውጤታማ ሥራዎች የተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሠላማዊት መኩሪያ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ በዘርፉ የነበሩ ማነቆዎች እየተፈቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ያሉ አምራቾች ምርታቸውን በሥፋት እንዲያመርቱ ምቹ እድል መፈጠሩን አውስተው ቢሮውም የምርት የግብይት ሰንሰለትን በማጠናከር ረገድ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በየአካባቢው ያሉ አምራቾች ምርታቸውን በስፋት ለገበያ የሚያቀርቡበትና ሸማቾችም የሀገራቸውን ምርት የመግዛት ፍላጎታቸው እንዲጨምር እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በባዛሩ ከ200 በላይ በተለያዩ የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርት ላይ የተሰማሩ አምራቾች እየተሳተፉ ሲሆን ይህም አምራቾች ምርታቸውን በማስተዋወቅ የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ ተሳትፏቸው እንዲያድግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከባዛሩ ተሳታፊዎች መካከል በማምረቻውና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የተሰማሩት ወይዘሮ ይርጋዓለም አስፋው፣ የአቮካዶ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ በመክፈት ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
የአቮካዶ ዘይት በውጭ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው መሆኑን ጠቁመው ከራሳቸው አልፈው አምራች አርሶ አደሮችና በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሌሎች ተሳታፊዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
በዛሬው ዕለይ የተከፈተው “የኢትዮጵያን ይግዙ” ኤግዚበሽን ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡