የደመወዝ ጭማሪው ሠራተኛውን ለበለጠ ምርታማነት የሚያነሳሳ ነው - ኮንፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የደመወዝ ጭማሪው ሠራተኛውን ለበለጠ ምርታማነት የሚያነሳሳ ነው - ኮንፌዴሬሽኑ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፡- የደመወዝ ጭማሪው ሠራተኛውን ለበለጠ ምርታማነት የሚያነሳሳ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ ገለጹ።
መንግሥት የቋሚ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ከመስከረም 2018 ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ጭማሪው የረጅም ጊዜ ጥያቄን የመለሰ ነው።
ይህ ጭማሪ የመንግሥት ሠራተኛውን የኑሮ ጫና በማቃለል በሥራው ላይ የበለጠ አምራች እንዲሆን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።
ጭማሪው በመንግሥት ደረጃ የነበረውን መነሻ ደመወዝ በአንድ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሰ መሆኑንም ገልፀዋል።
ጭማሪውን ተከትሎ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት መንግሥት ቁጥጥር ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በተጨማሪ ሸማቹ ማህበረሰብ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይፈጠር የበኩሉን አስተዋፅኦ መወጣት አለበት ብለዋል።
መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና ማቃለል የሚያስችል ውሳኔ በመወሰን ላደረገው የደመወዝ ጭማሪ ምስጋና አቅርበዋል።
የመንግሥት ሠራተኛውን የደመወዝ ማሻሻያ ተከትሎ በምርትና አገልግሎቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ መንግሥት ማሳሰቡ ይታወቃል።