በአማራ ክልል በዕውቀትና ክህሎት የታነፀ ትውልድ ለመገንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል -ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ

ባሕርዳር፤ ነሐሴ 17/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዕውቀትና ክህሎት የታነፀ ትውልድ ለመገንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ገለጹ። 

‎በቀጣይ አምስት ዓመታት ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ኢኒሼቲቭ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

‎የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በማጠቃለያው ላይ እንደገለጹት፤ ቴክኖሎጂን መፍጠር፣ መጠቀምና መተግበር የሚችል ትውልድ ለማመቻቸት ትኩረት ተሰጥቷል።  

‎ለዚህም በክልል ደረጃ ዛሬ ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው  የዲጂታል አማራ ኢኒሺቲቭ በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ዕውቀትና ክህሎት የላቁ ዜጎችን  ለማፍራት ታልሞ እንደሆነ  ተናግረዋል።

‎ክልሉ ባዘጋጀው የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማትና ዕድገት ዕቅድ ላይም በዲጅታል ቴክኖሎጂ የልማት ግቦችን ለማሳካት መመላከቱንም አንስተዋል።

‎ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም በሚተገበረው የዲጂታል አማራ ኢኒሸቲቭ ከ5 ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በማሰልጠን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙን አስታውቀዋል።  

የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በየደረጃው እያለው አመራር ራሱን ከወዲሁ አዘጋጅቶ መትጋት እንደሚጠበቅበት ጠቅሰው፤  በዘርፉ የተሰማሩ መምህራንም ለዲጂታል ኢኒሼቲቭ  ውጤታማነት ራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤  ወቅቱን የዋጁ፣ የተረዱ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ዜጎች ለማፍራት የዲጂታል አማራ ኢኒሸቲቭ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት በማስታጠቅ ልጆቹ በፍጥነት መረጃ አግኝተው የመማር ማስተማር ስራው ሳቢ እና ከዘመኑ ጋር አብረው የሚራመዱ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል።

የዜጎች የዲጂታል ዕውቀታቸው ጎልብቶ ክህሎታቸውን በማሳደግ ዓለም አቀፍ የኦን ላይን ቢዝነስ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት  መደገፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ለዚህም ክልሉ በአሁኑ ወቅት ዘርፈ ብዙ የዲጂታል ኢኒሺቲቮችን ስራ ላይ ለማዋልና  ከሰው ንክኪ ነፃ የሆኑ አገልግሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ቴክኖሎጂ እየዘመነና እየተስፋፋ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቤል ፈለቀ ናቸው።  


 

የትምህርት ተደራሽነትን በጥራትም ለማረጋገጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ማስፋፋት፤ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ማቅረብና የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ቅድሚያ ሰጥቶ ማሟላት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለሁሉም ተማሪዎች ተደራሽና ከባሕል ጋር ተዛማጅነት ያለው ዲጂታል ይዘት ያለው ቴክኖሎጂ ማዘጋጀት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም