ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ፤ የአህጉር በቀል መፍትሄዎች መድረክ 

በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን የአየር ንብረት በርቀት የሚያዩት ስጋት ሳይሆን የዕለት ተዕለት እውነታቸው ነው። 

በጎርፍ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች እና ተጠራርገው የሚወሰዱ ንብረቶች፣ በተከታታይ ድርቆች ምክንያት የሚያጋጥመው የምርታማነት መቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ከወለዳቸው ቀውሶች መካከል ይጠቀሳሉ። 
እነዚህ በተጨባጭ የዜጎችን ኑሮ እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች በአፍሪካ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስነ ምህዳር ላይ ለውጥ እንዲመጣ አስገድደዋል። 

የድህነት ምጣኔ እና የተፈናቃይ ዜጎች እየጨመረ መምጣት የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖዎችን በተግባር የገለጡ ጉዳዮች ሆነዋል።  
 

አፍሪካ ለዓለም የበካይ ጋዝ ልቀት ከአራት በመቶ በታች ድርሻ ቢኖራትም የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ከፍተኛ ቀንበር የሚያርፍባት አህጉር ሆናለች።

ከሳህል ቀጣና የበረሃማነት መስፋፋት እስከ ምስራቅ አፍሪካ ኃይለኛ ጎርፎች የአህጉሪቷ ዜጎች በጣም ውስን ድርሻ ባላቸው ጉዳይ የቀውሱ ከፍተኛ ሰላባ እየሆኑ ነው። 

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። 

እንደ ዓለም አቀፉ የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት መረጃ ከእ.አ.አ 1991 እስከ 2022 ባለው ሶስት አስርት ዓመታት ባሉ እያንዳዱ አስርት ዓመታት በአፍሪካ በአማካይ የ0 ነጥብ 3 ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት ጭማሪ ተመዝግቧል።

እ.አ.አ በ2024 የዓለም ሙቀት በ1 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ ጨምሮ በዓለም ታሪክ ከፍተኛው ሙቀት የተመዘገበበት ዓመት ነበር።

2024 በአፍሪካ የሙቀት መጠን 0 ነጥብ 86 በመቶ በመጨመር በአህጉሪቷ ታሪክ ከፍተኛው ሙቀት የተዘመገበበት ዓመት ሆኖም ተመዝግቧል።

ከሙቀቱ በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመር ባሻገር ድርቅ፣ ጎርፍ እና የምግብ ዋስትና ስጋት ላይ መውደቅ ሌሎች የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች ናቸው።

እ.አ.አ 2024 ደቡባዊ አፍሪካ ክፍል በቅርብ አስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ድርቅ አጋጥሟታል። በድርቁ ምክንያት ዛምቢያ እና ዚምባቡዌ የሰብል ምርታቸው በ50 በመቶ ቀንሷል።
በምስራቅ እና ማዕከላዊ አፍሪካ በቅርብ ጊዜ የተከሰቱ ከባድ ጎርፎች ሚሊዮኖችን አፈናቅለዋል፤ የዜጎች ህይወት አመሰቃቅላዋል መሰረተ ልማቶችንም አውድመዋል።

የዓለም አቀፉ ሜትሮሎጂ ድርጅት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካን ከሁለት እስከ አምስት በመቶ ጥቅል ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) ወጪ እየወሰደ ይገኛል።

አንዳንድ ሀገራት ለአየር ንብረት አስቸኳይ ምላሽ ዘጠኝ በመቶ ጥቅል ሀገራዊ ምርታቸውን ፈሰስ ያደርጋሉ።
አፍሪካ በየዓመቱ ከ30 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ለአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ አቅዶች ትግበራ ቢያስፈልጋትም ከዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ውስጥ የምታገኘው ገንዘብ ከአንድ በመቶ በታች ነው።

የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት የ2024 የአፍሪካ ሪፖርት የአፍሪካ የግብርና ምርታማነት ከእ.አ.አ 1961 በኋላ በ34 በመቶ መቀነሱን ይገልጻል።

የአፍሪካ ሀገራት ከውጭ ሀገራት ምግብ ለመግዛት የሚያወጡት 35 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወጪ እ.አ.አ በ2025 ማብቂያ ወደ 110 ቢሊዮን ዶላር ገደማ  ከፍ እንደሚል ገልጿል።

የበረሃማነት መስፋፋት፣ የብዝሃ ህይወት መመናመን፣ የጤና እክሎች፣ መፈናቀል እና የታሪካዊ ቅርሶች አደጋ ላይ መውደቅ አፍሪካ እየገጠሟት ያሉ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖዎች ውጤት ናቸው።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት በየዓመቱ 250 ቢሊዮን ዶላር ቢያስፈልጋትም እያገኘች ያለችው 30 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት አፍሪካ የጥያቄ አምሮት ኖሮባት የምታነሳው አጀንዳ ሳይሆን የፍትህ እና የህልውናዋ ጉዳይም ጭምር ነው። 

በአዲስ አበባ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አህጉሪቷ እየገጠሟት ካሉ አንገብጋቢ ፈተናዎችን በዘላቂነት መሻገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራል።

የሀገራት መሪዎች፣ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ወጣቶች እና የግሉ ዘርፍ በአንድነት ይወያያሉ።

በጉባኤው ላይ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በታዳሽ ኢነርጂ፣ ዘላቂ ግብርና እና ተፈጥሮ ተኮር መፍትሄዎች ጨምሮ በአፍሪካ ያሉ አረንጓዴ የመፍትሄ ሀሳቦች የበለ ማላቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀገራት ተሞክሯቸውን ያቀርባሉ።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ በየዓመቱ የሚያጋጥማትን የ220 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ አቅርቦት ክፍተት መሙላት እና አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀም ላይ ምክክር ይደረጋል።

በብራዚል ቤለም በሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) ጨምሮ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ድርድሮች ላይ የአፍሪካን ፍላጎቶች እና ጥቅሞች ማስጠበቅ የሚያስችል የጋራ እና ጠንካራ አቋም መያዝ ከጉባኤው የሚጠበቅ ውጤት ነው።

የአፍሪካ ሀገራት በጉባኤው ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የሚያስችሉ ተጨባጭና መሬት ላይ የወረዱ እቅዶቻቸው ላይ የሚያቀርቡ ሲሆን የገቡትን ቃል ኪዳን ወደ ተግባር መቀየራቸውን የሚከታተል የቁጥጥር ስርዓት ትግባራትን የሚያጠናክሩባቸው መንገዶችን በማቅረብ በአጠቃላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ቃልኪዳናቸውን ዳግም ያድሳሉ።
 

አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ገፈት ቀማሽ ሳትሆን የመፍትሄዎች እና የአይበገሬነት ስራዎች ማሳያም ናት። የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ እና አከባቢ ጥበቃ ስራዎች፣ የኬንያ የእንፋሎት እና የፀሐይ ኃይል ኢንሼቲቮች እንዲሁም የሞሮኮ ኑር ኦውርዛዛቴ የጸሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አረንጓዴ ልማት ሊሆን የሚችል ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የሚሳካ መሆኑን አፍሪካ ማረጋገጫ እንደሆነች በግልጽ የሚያመላክት ነው።

አፍሪካ ከዓለም ዋንኛ በካይ ጋዝ ለቃቂ ሀገራት ገንዘብ በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሀገር በቀል የፋይናንስ እና ሀብት ማሰባሰብ አቅማቸውን የበለጠ ማሳደግ ይጠበቅባታል።

የአዲስ አበባው ጉባኤም የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አቅርቦታቸውን እንዲጨምሩ ጥሪ የሚቀርብበት ነው።

አፍሪካውያን እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ከንግግር ያለፉ ሀገር በቀል መፍትሄዎችን በመተግበር አይበገሬ አቅም ሊገነቡ ይገባል።  

የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎችን ከዓለም አቀፍ አጋርነት ጋር ከማዛመድ አኳያ ያላው ሚና ወሳኝ የሚባል ነው።

ጉባኤው አፍሪካ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ትርክት ወደ መፍትሄ አፍላቂነት እና የግንባር ቀደም ሚና አበርካችነት ለመሸጋገር እንደ መስፈንጠሪያ የሚያገለግል ትልቅ እድል ነው።

የአዲስ አበባው ጉባኤ ከስብስባ ባለፈ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ቆርጣ ለተነሳችበት የተግባር ምላሽ ጉዞ እና የዓለም አቀፍ ተጠያቂነት መረጋገጥ የጋራ ትግል ውስጥ ትልቅ እጥፋት ሊሆን ይችላል። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም