በመዲናዋ በቅርቡ ስራ የጀመሩ ጤና ጣቢያዎች ጥራት ያለው ህክምና እንድናገኝ አስችለውናል - ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በቅርቡ ስራ የጀመሩ ጤና ጣቢያዎች ጥራት ያለው ህክምና እንድናገኝ አስችለውናል - ተገልጋዮች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ስራ የጀመሩ ጤና ጣቢያዎች በአቅራቢያቸው ጥራት ያለው ህክምና ለማግኘት እንዳስቻላቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተገልጋዮች ተናገሩ።
በአዲስ አበባ ከተማ በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ አዲስ የተገነቡ፣ ማስፋፊያና ዕድሳት የተደረገላቸው 22 ጤና ጣቢያዎች ሐምሌ 19 ቀን 2017 ዓ.ም መመረቃቸው ይታወሳል።
አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት ጤና ጣቢያዎች መካከል በአስኮ አዲስ ሰፈርና በቂርቆስ ጤና ጣቢያዎች ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች በተቋማቱ በአቅራቢያቸው በፍጥነት የህክምና አገልግሎት ለማግኘት አስችለዋቸዋል።
በአስኮ አዲስ ሰፈር ጤና ጣቢያ ሲታከሙ ያገኘናቸው ነኢማ ምህረት እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በአቅራቢያቸው ጤና ጣቢያ ባለመኖሩ ህክምና ለማግኘት ወደሌላ አካባቢ መሄድ ይጠበቅባቸዋል።
አሁን ላይ ግን ጥራት ያለው ህክምናን በአቅራቢያቸው ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ሌላው በጤና ጣቢያው ሲገለገሉ ያገኘናቸው ተካልኝ ሄርጶ፤ የጤና ጣቢያው ስራ መጀመር ርቀት ሳይጓዙና የትራንስፖርት ወጪ ሳያወጡ ህክምናን እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
የጤና ጣቢያው ስራ መጀመር በቅርበትና በጥራት የህክምና አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ያለችው ደግሞ ቅድስት ማዕረጉ ናት።
በቂርቆስ ጤና ጣቢያ ያነጋገርናቸው ቀጄላ ዱጋሳ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ጤና ጣቢያው ውስን አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር አንስተው፤ አሁን ላይ በርካታ አገልግሎቶችን እያገኙ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
አሁናዊ ሁኔታውን ከቀድሞው ጋር ማነፃፀር የማይቻል ነው ያሉት አቶ አረጋ አበበ፤ ጤና ጣቢያው ወረቀት አልባ፣ ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።
በጤና ጣቢያው አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ለተገልጋይ ብቻ ሳይሆን ለባለሙያውም ምቹ ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ።
በቂርቆስ ጤና ጣቢያ የተመላላሽ ህክምና ቡድን መሪ ድንበሩ መኮንን ከዚህ ቀደም ጤና ጣቢያው ምቹ እንዳልነበርና አሁን ላይ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ባለሙያው በተነሳሽነት እንዲሰራ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በቂርቆስ ጤና ጣቢያ የታካሚዎች ልየታ፣ ምዝገባና ክፍያ ቡድን መሪ ደስታ ከበደ፤ ከዚህ ቀደም በአንድ ክፍል ውስጥ ሁለት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አውስተው፤ አሁን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎቶችን ወደመስጠት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።
የአስኮ አዲስ ሰፈር ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር የሱፍ ቱግባር እንደተናገሩት፤ ጤና ጣቢያው ተመርቆ ስራ ከጀመረበት አንስቶ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ በጥራት እየሰጠ ይገኛል።
በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደራጀ የማዋለጃ ክፍል፣ የህፃናት ህክምና፣ የጥርስ ህክምናና ሌሎች አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ በቅርበት እየሰጠ መሆኑን በመጥቀስ።
የቂርቆስ ጤና ጣቢያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አበባ ምትኩ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ጤና ጣቢያው ለባለሙያም ሆነ ለታካሚ የማይመች እንደነበር ነው ያስታወሱት።
አሁን ላይ በጤና ጣቢያው በርካታ ባለሞያዎች ያሉት በመሆኑ የታካሚዎችን ሪፈራል የሚቀንስ አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
በአማካይ በቀን እስከ 400 የሚደርስ ተገልጋይ ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልፀው፤ ከአጠቃላይ ህክምና ባለፈ የጥርስ፣ የቆዳና ዓይን ህክምናዎችን ጭምር እየሰጠ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ እንደገለጹት፤ 13ቱ ማስፋፊያ የተደረገላቸው፣ ዘጠኝ አዲስ የተገነቡ ጤና ጣቢያዎች ወደ ስራ ገብተዋል።
አንድ ጤና ጣቢያ እስከ 40ሺህ ተገልጋይ ያስተናግዳል ተብሎ እንደሚታመን ተናግረው፤ አሁን ላይ አገልግሎት የጀመሩ ጤና ተቋማት ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሳደግ እንዲሁም ነባር አገልግሎቶችን በላቀ ደረጃ ለመስጠት የሚያስችል ነውም ብለዋል።