አሸንዳ- የፍቅርና የሰላም አጀንዳ - ኢዜአ አማርኛ
አሸንዳ- የፍቅርና የሰላም አጀንዳ

በአማረ ኢታይ
የሴቶች በተለይም የልጃገረዶች በዓል መሆኑ የሚነገርለት የአሸንዳ በዓል ለማክበር አመቱ እስከሚደርስ ድረስ በጉጉትና በናፍቆት ይጠበቃል። አሸንዳ ይዋቡበታል፣ ቁንጅና ጎልቶ ይወጣበታል፣ ልጃገረዶችና ሴቶች ተሰባስበው የሚያዜሙበት፣ በስጦታ ጭምር የሚታጀብ ልዩ እና ውብ የአደባባይ በዓል ነው።
የአሸንዳ በዓል ሲቃረብ በተለይ ልጃገረዶች ቀደም ብለው የመዋቢያ ጌጣጌጦችንና አልባሳትን አዘጋጅተው የበዓሉን መድረስ ይጠባበቃሉ። እለቱም ሲደርስ በተለየ ሁኔታ ተውበውና ደምቀው ከበሮ ይዘውና በጣእመ ዜማ ታጅበው ወደ አደባባይ በመውጣት ያከብሩታል።
በዚህም መሰረት ትግራይ የአሸንዳ በዓል በየዓመቱ ከነሃሴ 16 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በደማቅ ስነ ስርአት ይከበራል። እለቱ የልጃገረዶች የነፃነት ቀንም በመሆኑ የቤተሰብ፣ የዘመድ አዝማድ ቁጣ እና ይህን አድርጊ ይህን አታድርጊ የሚል ትእዛዝ እና ጫና አይኖርም። በመሆኑም አሸንዳ - የነፃነት፣ የፍቅርና የሰላም አጀንዳ ያነገበ በመሆኑ ከልጅ እስከ አዋቂ በየአመቱ በጉጉት የሚጠበቅ ደማቅ በዓል ነው።
የአሸንዳ ልጆች ከበዓሉ ዋዜማ ጅማሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ በየሰፈራቸው በቡድን በቡድን ተሰባስበው የሚጫወቱበት በመሆኑም የህብረት፣ የፍቅር፣ የሰላምና የአብሮነት ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል።
ወላጆቻቸው አነስተኛ ገቢ ያላቸው ልጃገረዶችም ከእኩዮቻቸው፣ ከዘመድ አዝማድ እና ከጎረቤቶቻቸው የመዋቢያ ጌጣጌጦችን፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሶችን ወስደው በዓሉን በደስታ የሚያሳልፉ ይሆናል። በዚህም መሰረት በዓሉ የመረዳዳት፣ የትብብርና ችግርን በመተጋገዝ ማለፍ እንደሚቻል የሚያመላክት ልዩ በዓል ነው። በዚሁ መሰረት የ2017 ዓ.ም የአሸንዳ በዓል በደማቅ ስነ ስርአት በመከበር ላይ ይገኛል። የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ በርካታ ቱሪስቶች ልጃገረዶችና ሌሎችም የበዓሉ ታዳሚዎች በተገኙበት በመከበር ላይ ነው።
በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ውብ የሆኑ መገለጫዎች ያሏት ሀገር በመሆኗ አጉልተንና ለዓለም አስተዋውቀን የውበታችን ማሳያ እና የሃብት ምንጭ ጭምር ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል። የአሸንዳ በዓልን እሴት በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ ተቀናጅተን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚከበሩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶችን በማክበር ጠብቆ ማዝለቁ እንዳለ ሆኖ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን የማልማትና ታሪካዊ ቅርሶችን መጠበቅም ትኩረታችን ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የአሸንዳ በዓልን በድምቀት እያከበረ ለሚገኘው ለመላው የትግራይን ህዝብ በተለይም ለልጃገረዶች የሰላምና የፍቅር በዓል እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል።
"የአሸንዳ በዓልን ማስዋብና ማድመቅ ለሰላምና ለአንድነት ያለንን መልካም ፍላጎትና ምኞት ማሳያ ነው። ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና እንዲለማ እንሰራለን።" በማለት መልእክታቸውን ያጋሩት ደግሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ናቸው።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አፅበሃ ገብረእግዛብሄር በበኩላቸው፣ ባህላዊ ይዘት ያለው የአሸንዳ በዓል ሳይበረዝ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የክልልና የፌዴራል መንግስታት በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
በመቀሌ ከተማ እየተከበረ ባለው የአሸንዳ በዓል ከባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ በተጨማሪ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እና ሌሎችም ታድመዋል። አሸንዳ - የነፃነት፣ የፍቅርና የሰላም አጀንዳ ሆኖ መከበሩንም ቀጥሏል።