በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መሰረታዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት እያገኘን ነው - የስልጠናው ተሳታፊዎች

ጅማ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መሰረታዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት እያጎለበቱ መሆኑን በጅማ ከተማ ስልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች እና ተማሪዎች ተናገሩ።

በጅማ ከተማ ስልጠናውን እየተከታተሉ የሚገኙ የመንግሰት ሰራተኞች እና ተማሪዎች ከስልጠናው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ እየሰለጠነ የሚገኘው ምትኩ አብደታ ስልጠናው በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዙሪያ ተጨባጭ እውቀት መጨበጥ እንዳስቻለው ተናግሯል።

በተመቻቸላቸው የአትዮ ኮደርስ ስልጠናም አራቱንም ኦንላይን ስልጠናዎች መውሰዳቸውን ጠቅሶ በተለይም የዳታ ሳይንስና የኤ.አይ (AI) ኮርሶች ትልቅ አቅም እንደፈጠሩለት ገልጿል።

ሌላው የመንግስት ሰራተኛ አብዱሰላም ጠይብ፤ በክረምቱ ወራት ስልጠናውን ተከታትሎ መጨረሱ ክህሎቱን እንዳዳበረለት ይገልጻል።

ስልጠናው ለተለያዩ የሙያ አይነቶች የሚያግዝ በመሆኑ ስልጠናውን ያልወሰዱ የመንግስት ሰራተኞች ቢወስዱ ትልቅ ጥቅም ያገኛሉ ብሏል።

በወሰደው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተሻለ እውቀት ማግኘቱን የገለጸው ደግሞ ተማሪ አባስ አለሙ ሲሆን ወደ ፊት በዚህ ዘርፍ የራሱን የስራ እድል ለመፍጠር ማቅዱን ተናግሯል።

በስልጠና ቆይታው ያገኘውን እውቀት እና ክህሎት ተጠቅሞ በሞባይል መተግበርያ ዙሪያ ስራዎችን ለመስራት እንደሚጥር ነው የተናገረው።

ስልጠናው በትምህርት፣ በስራ እድል ፈጠራና ክህሎት እንዲሁም በሲቪል ሰርቪስ ጽህፈት ቤቶች አስተባባሪነት እየተሰጠ መሆኑም ተገልጿል።

ስልጠናውን ከሚያስተባብሩ ጽህፈት ቤቶች አንዱ የሆነው የጅማ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ጽህፈት ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የስራ ሂደት መሪ ናስር አማን፤ ስልጠናው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትን በማሳደግ የሰራተኛውን የመፈጸም አቅም ለማጎልበት ይረዳል ብለዋል።

ጽህፈት ቤቱ በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ የመንግስት ሰራተኞች፣ ተማሪዎችና መምህራን ስልጠናውን እንዲወስዱ አስፈላጊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ስልጠናው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም