ቀጥታ፡

ምክክሩ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ስለሚያመጣ በሂደቱ የድርሻችንን እንወጣለን

ደሴ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክሩ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ ስለሚያመጣ በሂደቱ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን "የወጣቶች ሚናና ተሳትፎ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሀሳብ ከአማራ ወጣቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።


 

ወጣቶቹ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት፤ ምክክሩ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄን ስለሚያመጣ በሂደቱ የድርሻችንን እንወጣለን።

የደሴ ከተማ ነዋሪና የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ቢላል ወዳጆ በኢትዮጵያ ዘላቂ አንድነትና ሰላም ለመፍጠር ምክክሩ ታላቅ ተስፋን ይዞ መጥቷል ነው ያለው።

በሀሰት መረጃ ሳልደናገር ከውይይቱ ያገኘሁትን እውቀት ለሌሎች ግንዛቤ በመፍጠርና ሀሳብ በማመንጨት የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብሏል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ነዋሪ ወጣት ፍሬዘር ሀይሉ በበኩሉ ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆንና የኢትዮጵያ ሁለተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ የድርሻዬን ለመወጣት ቁርጠኛ ነኝ ሲል ገልጿል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ቃልኪዳን ታደሰ አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን የምክክር ኮሚሽኑን በማገዝና በመደገፍ የምክክሩ ዓላማ እንዲሳካ እንሰራለን ብላለች።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው አካታች፣ አሳታፊና ተዓማኒ ምክክር በማካሄድ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ሀገር ተረካቢ ወጣቶች በሚካሄደው ምክክር ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ፣ የዳበሩ ሀሳቦችን በማመንጨት፣ አጀንዳቸውን በማስያዝና ምክረ ሀሳብ በመስጠት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም