የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታው ይዞታችንን በተሻለ አልምተን ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል-አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታው ይዞታችንን በተሻለ አልምተን ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል-አርሶ አደሮች
ደሴ ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፡- የተሰጣቸው የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ይዞታቸውን በተሻለ ለማልማትና ተጨማሪ ሃብት ለመፍጠር ምቹ መደላደል እንደሆናቸው በደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
በደቡብ ወሎ ዞን በ2017 የበጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ሁለተኛ ደረጃ የመሬት ማረጋገጫ ካርታ መስጠት መቻሉን የዞኑ መሬት መምሪያ ገልጿል።
በዞኑ ተሁለደሬ ወረዳ የ011 ቀበሌ አርሶ አደር አራጋው ሰይድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በይዞታ መሬታቸው አዋሳኝ አካባቢ ልኬቱ በትክክል ስለማይታወቅ ችግር ይገጥማቸው ነበር።
ይህም የጊዜው ከአዋሳኝ ባለ ይዞታ ባለቤቶች ጋር በመገፋፋት ጠብና ጭቅጭቅ እየገጠማቸው መሬታቸውን ተንከባክበውም ለማልማት እንዳይነሳሱ አግዷቸው እንደቆዩ አንስተዋል።
ዘንድሮ የይዞታቸውን ወሰንና ልኬታውን በትክክል ያስቀመጠ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በማግኘታቸው ችግሩን በመፍታት የተሻለ ለማልማት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም መሬታቸውን አሲይዘው 80 ሺህ ብር በመበደር ለልጃቸው የስራ እድል ለመፍጠር እንዳገዛቸውም አንስተዋል።
በለጋምቦ ወረዳ 023 ቀበሌ አርሶ አደር አህመድ አሊ በበኩላቸው፤ የተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሬታቸውን በአግባቡ ማልማትና መጠቀም እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ፈጠሮልናል ብለዋል።
የይዞታችንን ካርታ አስይዘውም ከተለያዩ ተቋማት ገንዘብ ለመበደር፣ ለሌሎች ዋስ ለመሆንና ተጨማሪ ሀብት ለማፍራትም እንዲሁ።
በደቡብ ወሎ ዞን መሬት መምሪያ የገጠር መሬት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ምሳው አክቤ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ61 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጥቷል።
በዚህም የአርሶ አደሩን የይዞታ መሬት በሳይንሳዊ መንገድ በመለካትና አዋሳኙን በትክክል በማስቀመጥ መሰራቱን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ካርታውን መውሰዳቸው በወሰንና ሌሎች ምክንያቶች ይፈጠሩ የነበሩ አለመግባባቶችን ማስቀረት ችሏል፤ ቅሬታ ሲፈጠርም በቀላሉ ማስተካከል አስችሏል ብለዋል።
ካርታው ለአርሶ አደሮች በዋስትና የመበደር መብት በመስጠቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 785 አርሶ አደሮች ከ57 ሚሊዮን ብር በለይ ብድር በማግኘት እንዲጠቀሙ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
ከመሬት መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በደቡብ ወሎ ዞን ባለፉት ዓመታት በተከናወነው ስራ ለ378 ሺህ 447 አርሶ አደሮች ሁለተኛ ደረጃ የመሬት ማረጋገጫ ካርታ መስጠት ተችሏል።