ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት ላይ ያተኮረ የኦንላይን ቢዝነስ ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል - የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ

ባሕርዳር፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ወጣቶችን በዲጂታል ኢኒሼቲቭ የኦንላይን ቢዝነስ ስልጠና ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

‎"በዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት የታነፀ ትውልድ ለአሻጋሪና ዘላቂ ዕድገት" በሚል መሪ ሃሳብ የዲጂታል ኢንሼቲቭ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

‎በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

‎በማስጀመሪያ መድረኩ ላይ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቤል ፈለቀ እንደገለጹት፤ እስከ 2022 ዓ.ም ከ5 ሚሊዮን በላይ የክልሉን ወጣቶች በዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት ላይ ያተኮረ የኦንላይን ቢዝነስ ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል።

‎ለዚህም የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በሂደቱም በትምህርት ላይ ለውጥ ለማምጣትና የኦን ላይን የስራ ዕድል ፈጠራን ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

‎የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን የማስፋፋት፣ የፈጠራ ሃሳብና ችግር ፈቺ ትውልድን ለመገንባት እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።


 

‎በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ‎የዲጂታሉ ዓለም በፈጠነ የዕድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዘመኑን የዋጀ ትውልድ ለመገንባት መምህራን ራሳቸውን ሊያዘጋጁ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ለዚህም የሚያግዙ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪ ተኮር የማስተማሪያ ሞጅሎች እየተዘጋጁ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

‎ስልጠናው የኦን ላይን ቢዝነስ ላይ አተኩሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚሰጥ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም