የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬም ቀጥሎ ይውላል - ኢዜአ አማርኛ
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬም ቀጥሎ ይውላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ማንችስተር ሲቲ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ በኢትሃድ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ባለሜዳው ማንችስተር ሲቲ በመጀመሪያ ሳምንት ከሜዳው ውጪ ዎልቨርሃምፕተን ዎንድረርስን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ዓመቱን በድል ጀምሯል።
የሰሜን ለንደኑ ቶተንሃም ሆትስፐርስ በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታው በርንሌይን 3 ለ 0 ረቷል።
ሁለቱ ክለቦች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚያደርጓቸው የሊጉ ጨዋታዎች አዝናኝ፣ ጠንካራ ፣ በበርካታ ግቦች የታጀበ እንቅስቃሴ እና ለተመልካች ሳቢ ፉክክር እያደረጉ ይገኛል።
በቡድኖቹ ያለፉት 10 የሊግ ግንኙነቶች 32 ግቦች መቆጠራቸው የፉክክራቸው ማሳያ ነው።
ቦርንማውዝ ከዎልቨርሃምፕተን ዎንድረርስ፣ በርንሌይ ከሰንደርላንድ እና ብሬትንፎርድ ከአስቶንቪላ በተመሳሳይ ከቀኑ ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ አርሰናል በኤምሬትስ ስታዲየም ሊድስ ዩናይትድ ያስተናግዳል።
አርሰናል በመጀመሪያው ጨዋታ ታሪካዊ ባለንጣውን ማንችስተር ዩናይትድን ከሜዳው ውጪ 1 ለ 0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ ተመልሷል።
ከሁለት ዓመት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሰው ሊድስ ዩናይትድ በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታ ኤቨርተንን 1 ለ 0 በማሸነፍ አጀማመሩን አሳምሯል።
ባለሜዳው አርሰናል ጨዋታውን የማሸነፍ ሰፊ ግምት ወስዷል።