ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ተወዳዳሪነት የሚያዘምን ስኬት ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2017(ኢዜአ)፡-በ2017 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ተወዳዳሪነት የሚያዘምን ስኬት መመዝገቡን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር "በተሳለጠ ንግድ ወደ ሚጨበጥ ሀገራዊ ተስፋ" በሚል መሪ ሃሳብ የ2017 በጀት ዓመት ሀገራዊ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር የዘርፍ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።


 

በዚሁ ወቅት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፥ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ለኢትዮጵያ የንግዱ ሥርዓት የተስፋ ብርሃን የፈነጠቁ አሻጋሪ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃም የምርት አቅራቢና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ የሚያገናኙ ከ1ሺህ 500 በላይ ማዕከላትን በመገንባት ወደስራ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱም የቅዳሜና እሁድ ግብይት ማዕከላትን ማስፋፋት የሚያስችል ስኬት መመዝገቡን አስረድተዋል።

ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደንበኞችም በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያን የንግድ ስርዓት የማዘመን ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በወጪ ንግድም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን ያበሰረ የስምንት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።

በውጭ ምንዛሬ ግኝት ለተመዘገበው ስኬትም የግብርና፣ የማዕድን፣ በኢንዱስትሪና ሁሉም ዓይነት የወጪ ንግድ ዘርፎች ከፍተኛ መነቃቃት እየተፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም በወጪ ንግድ ምርቶች የተመዘገቡ ስኬቶችን በማላቅ ዘጠኝ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማስገኘት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ሁለት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የድርድር ሂደትም ለመቋጨት በተደረገው ጥረትም በ2017  በጀት ዓመት ስኬታማ ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

በአምስተኛው የስራ ቡድን ስብሰባም የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት የሚያሳካ ተሳትፎ በማድረግ በመስከረም 2018 ዓ.ም በሚካሄደው ስድስተኛው የስራ ቡድን ስብሰባ  የተሟላ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ባለብዙ ወገን የንግድ ትስስር ሥርዓትም የአፍሪካን አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ስራ ላይ ለማዋል ብሔራዊ የትግበራ ስትራቴጂ ዝግጁ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም የንግድ ስምምነቱን የትግበራ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ በመስከረም 2018 ዓ.ም ላይ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የዝግጅት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተመረቀው የጥራት መንደርም በብዙ ሚሊዮን ቶን የሚገመት የወጪና ገቢ ምርት ቁጥጥር በማድረግ ለጥራት አቅርቦት ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።  

በሚኒስትር ዴኤታ የሚመራ የኢ-ኮሜርስ ዘርፍ ተቋቁሞ ወደ ትግበራ ማስገባት የሚያስችል ስራ መሰራቱን አንስተዋል።

የክልል ንግድ ቢሮ ኃላፊዎችም የበጀት ዓመቱን የአፈጻጸም ሪፖርት በማቅረብ ለ2018  በጀት ዓመት በተያዙ ዕቅዶች ላይ የመግባቢያ ስምምነት በማድረግ የዘርፎች ጉባኤው እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም