ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ለጣውላና ለከሰል ፍጆታ የሚውሉ የዛፍ ዝርያዎችን እያስፋፋ ነው

አርባምንጭ ፤ ነሐሴ 16/2017(ኢዜአ)፡-  አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለጣውላ እና ለከሰል ፍጆታ የሚውሉ ግራርን ጨምሮ የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ።

በደጋ እና በወይና ደጋ የሚለሙ የግራርና ለጣውላ አገልግሎት የሚውሉ የዛፍ ዝሪያዎች ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ተካሄደ።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል (ዶ/ር) በወቅቱ ለኢዜአ እንዳሉት ፤ ዩኒቨርሲቲው የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።


 

ከዓለም አቀፍ የደን ምርምር ማዕከል ጋር በትብብር የሚሠራው የዕፅዋት ፕሮጀክት አርሶ አደሩ በራሱ ማሳ በሚያለማቸው ችግኞች ጣውላ እና ከሰል በማምረት ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የማህበረሰቡን የገቢ ምንጭ ከማሳደግ ባለፈ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውና የዛፎቹን ልማትና አመራረት ሂደት ለአርሶ አደሮች ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የደጋና ወይና ደጋ አየር ፀባይ የሚስማማቸው የግራርና የባህር ዛፍ ዝሪያዎች በአጭር ጊዜ የሚደርሱ በመሆናቸው አርሶ አደሩ ከሰብል በተጓዳኝ በማልማት የገቢ አቅሙን እንደሚያሳድግ የምርምርና የትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት  ተክሉ ወጋየሁ (ዶ/ር) ተናግረዋል።


 

ከዚህ ጋር በተያያዘ በደኖች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቅረፍ መፍትሄ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት እስኪረጋገጥ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣ  ጠቁመዋል።

የዓለም አቀፍ የደን ምርምር ማዕከል ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አገና አንጁሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ በሌሎች ሀገራት  ከፍተኛ ጠቀሜታ ያስገኙ ዘጠኝ ዓይነት የባህር ዛፍ እና ሦስት ዓይነት የግራር ዝርያዎች የሙከራ ተከላ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በዕፅዋቶች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ማንኛውንም በሽታ እና ተባዮችን  ለመቆጣጠር በቂ ዝግጅት መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም