የቆዳ በሽታ አይነቶች … - ኢዜአ አማርኛ
የቆዳ በሽታ አይነቶች …
ከ3 ሺህ የሚልቁ የቆዳ በሽታ(ህመም) ዓይነቶች እንዳሉ ይነገራል።
በቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ፣ እባጭ እንዲሁም ማንኛውም ነገር የቆዳ ህመም ተብሎ እንደሚጠራ በአለርት ሆስፒታል የቆዳና አባላዘር ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዓለምፀሐይ ጌታቸው ይገልጻሉ።
እስከ አሁን በዓለም ላይ ከ3ሺህ የሚበልጡ የተረጋገጡ የቆዳ ህመም ዓይነቶች እንዳሉ ጠቁመው፤ ምርምር ላይ ያሉ ኬዞችም ስላሉ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ነው ያመላከቱት።
በስፋት ከተለመዱ የቆዳ ህመም ዓይነቶች መካከልም፤ አልማዝ ባለጭራ፣ ብጉር፣ አለርጂ፣ የሥጋ ደዌ እና ሌሎችንም ይጠቀሳሉ።
በተለይም ከክረምት ወቅት ጋር በተያያዘ ከሚከሰቱ የቆዳ ህመሞች መካከል በአልማዝ ባለጭራ ትንኝ ምክንያት የሚከሰተው አልማዝ ባለጭራ ህመም አንዱ መሆኑን አንስተዋል።
በነፍሳቷ ምክንያት የሚመጣው የቆዳ በሽታ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል እንደሚያጠቃ የሚገልጹት የሕክምና ባለሙያዋ፤ በተለይም በቅዝቃዜና በክረምት ወቅት ለመራባት ምቹ ስለሚሆንላት በሽታው በስፋት እንደሚከሰት ያስረዳሉ።
በመኝታ ወቅት በልብስ ባልተሸፈኑ የሰውነት ክፍሎች ላይ አልማዝ ባለጭራ ስትሄድ ለማንሳት ስንሞክር በምትጨፈለቅበት ጊዜ የምታመነጨው ኬሚካል በቆዳ ላይ መቆጣት(ህመም) እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።
ህመሙም ከተወሰኑ ቀናት እስከ ሣምንታት በቆዳ ላይ ሊቆይ እንደሚችል ነው የተናገሩት።
ዝናባማ ወቅት መሆን፣ አትክልት በበዛበት ግቢ መኖር፣ በምሽት መብራት አብርቶ መተኛት ለአልማዝ ባለጭራ ነፍሳት ምቹ ሁኔታዎች ስለሆኑ በህመሙ የመጠቃት ዕድሉ ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።
ህመሙ ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከልም፤ ነፍሳቷ በተጨፈለቀችበት የቆዳ ክፍል ላይ የማቃጠል፣ የመቆጥቆጥ፣ የመቅላት፣ ውኃ የቋጠሩ ትንንሽ መግል የያዙ እባጮች መኖር የመሳሰሉትን ዘርዝረዋል።
እነዚህን ምልክቶች ተከትሎም ቁስሉ ያለበት ቦታ ላይ ለተጨማሪ ማመርቀዝ (የባክቴሪያ ኢንፌክሽን)፣ ሰፋ ላለ ቁስል መጋለጥ ብሎም ቁስሉ ከዳነ በኋላ ጠባሳ(ጥቁረት) ሊኖር እንደሚችል ያነሳሉ።
የዚህን ህመም መኖር የቆዳ ሕክምና ባለሙያዎች ካረጋገጡ በኋላ አስፈላጊውን ሕክምና እንደሚሰጡም ነው ዶክተር ዓለምፀሐይ ጌታቸው የገለጹት።
ለምሳሌ ቀለል ያለ በቆዳ ላይ ያለ መቅላትና ሽፍታ ብቻ ከሆነ በሚቀቡ መድኃኒቶች ማከም እንደሚቻል ገልጸው፤ ከዚህ ያለፈ ጠንከር ያለ የጎንዮሽ ጉዳት ካለም ተገቢውን ሕክምና እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።
በክረምት ወቅት ነፍሳቷ ለመራባት ምቹ ሁኔታ ስለምታገኝ ይህን በመገንዘብ አትክልት በሚበዛባቸው አካባቢዎች የሚኖር ሰው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ከተቻለም አትክልቶቹን ማስወገድ፣ በመኝታ ጊዜም የሰውነት ክፍሎችን የሚሸፍኑ ሙሉ ልብሶችን መልበስ፣ በተቻለ መጠን መሬት ላይ ከመተኛት መቆጠብ፣ መብራት አጥፍቶ መተኛት፣ ነፍሳቷን መከላከል የሚያስችል አጎበር መጠቀም የሚሉትን በመከላከያ መንገድነት ዘርዝረዋል።
ነፍሳቷን በቤት ውስጥም ሆነ በሰውነት ክፍላችን ላይ በምናገኛት ጊዜ ሰውነታችንን ሳትነካ በጥንቃቄ ማስወገድ፣ በሆነ አጋጣሚ ሰውነታችን ላይ ከተጨፈለቀችና ኬሚካሏ ቆዳችንን ከነካው ደግሞ ወዲያውኑ በውኃ መታጠብ እንደሚገባ መክረዋል።