የዋናውን ጉባኤ አጀንዳዎች የሚቀርጹት የቅድመ-ጉባኤ ውይይቶች - ኢዜአ አማርኛ
የዋናውን ጉባኤ አጀንዳዎች የሚቀርጹት የቅድመ-ጉባኤ ውይይቶች
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ይህ ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂነቷ እየበረታ ለመጣባት አፍሪካ በወሳኝ ሰዓት የሚደረግ ሁነት ነው ማለት ይቻላል።
ከዋናው ጉባኤ ቀደም ብሎ ለግዙፉ አህጉራዊ ሁነት መደላድል የሚፈጥሩ ቅድመ ጉባኤ ውይይቶች ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳሉ።
በውይይቶቹ መንግስታት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የልማት አጋሮችና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ይሳተፋሉ። ይህም ሁሉን አሳታፊ ምክክር ለማድረግ ለተያዘው እቅድ እንደ መንደርደሪያ የሚያገለግል ነው።
አካባቢያዊ መፍትሄዎችን ከአህጉራዊ የአየር ንብረት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል።
የመግቢያ ምክክሮቹ ማህበረሰብ ተኮር መፍትሄዎች ጎልተው የሚሰሙበት፣ የአፍሪካ የጋራ አጀንዳ የሚቀረጽበት እንዲሁም ሀገራት ለአየር ንብረት ፋይናንስ፣ የማጣጣሚያ እቅድ እና ዘላቂ እድገት ሀገራት ጠንካራ ቃል ኪዳኖችን የሚገቡበት መሆኑን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።
የቅድመ-ጉባኤ ምክክሩ ከነሐሴ 26 እስከ ጳጉሜን 1 2017 ዓ.ም ከሚቆየው የአፍሪካ የአየር ንብረት ሳምንት (CW2) ጋር የተሳሰረ ነው።
ሳምንቱ መንግስታት፣ የልማት አጋሮች እና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የአየር ንብረት የመከላከል ስራን ተጨባጭ በሆኑ የትግበራ መንገዶች ውጤታማ ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ምክክር ይደረጋል።
አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ውይይቶች ላይ ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆኑና በኢነርጂ ሽግግር፣ የማጣጣሚያ እቅዶች ትግበራ፣ አይበገሬነት እና ፋይናንስ አፍሪካ መር መፍትሄዎች ጎልተው እንዲታዩ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላክል ገቢራዊ እያደረገቻቸው ያሉ ስራዎችን በአየር ንብረት ለውጥ ሳምንቱ ላይ ታቀርባለች።
ቅድመ ጉባኤው ድምጾች ከታች ወደ ላይ እንዲሰሙ በማድረግ የዋና ጉባኤ ውሳኔዎች የዜጎችን ነባራዊ እውነታዎች የሚያንጸባርቁ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ዘላቂነት ያለው የበርካታ ባለድርሻ አካላት አጋርነቶችን በማጠናከር የተቀናጀ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ማዕቀፍም ነው።
በተለይም አካባቢያዊ እውነታዎች እና ዓለም አቀፍ ማዕቀፎች መካከል ያለውን የተጣጣሚነት ክፍተት በምን አይነት መልኩ መሙላት ይቻላል? የሚለው ጉዳይ የመፍትሄ ሀሳቦች ይመነጩበታል።
ሀገር በቀል የፋይናንስ አማራጮች ከውጭ ድጋፍን በማጣመር ውጤታማ የአየር ንብረት ለውጥ የመከላከል ስራ ማከናወን በቅድመ ጉባኤው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
የካርቦን ገበያ፣ ጤና እና አየር ንብረት፣ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ አረንጓዴ ኢኖቬሽን፣ አረንጓዴ እድገት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎች ተጣጣሚነትና ቀጣናዊ ትብብር ውይይት ከሚደረግባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ዋና ጉባኤው በአየር ንብረት ፋይናንስ፣ ኢኖቬሽን፣ በማይበገር አቅም ግንባታ፣ በብሄራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅዶች ትግበራና ሌሎች የሚወያይባቸውን አጀንዳዎች የሚቀርጽ መሆኑን ህብረቱ ገልጿል።
በአጠቃላይ በቅድመ ጉባኤው ላይ የሚንሸራሸሩ ሀሳቦች ለሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡበት መሰረት የሚጥል ነው።